ሆሴዕ 1

1 በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያን፣ በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን እንዲሁም በእስራኤል ንጉሥ በዮአስልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣውየእግዚአብሔርቃል ይህ ነው፤

የሆሴዕ ሚስትና ልጆቹ

2 እግዚአብሔርበሆሴዕ መናገር በጀመረ ጊዜ፣እግዚአብሔር“ምድሪቱከእግዚአብሔርተለይታ ታላቅ ምንዝርና እያደረገች ስለ ሆነ፣ ሄደህ አመንዝራ ሴት አግባ፤ የምንዝርና ልጆችንም ለራስህ ውሰድ” አለው።

3 ስለዚህ እርሱ የዴቤላይምን ሴት ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት።

4 እግዚአብሔርምሆሴዕን እንዲህ አለው፤ “በኢይዝራኤል ስለ ተፈጸመው ግድያ የኢዩን ቤት በቅርቡ ስለምቀጣና የእስራኤልንም መንግሥት እንዲያከትም ስለማደርግ፣ ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው።

5 በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ፣ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ።”

6 ጎሜር እንደ ገና ፀነሰች፤ ሴት ልጅም ወለደች፤እግዚአብሔርምሆሴዕን እንዲህ አለው፤ “ይቅር እላቸው ዘንድ ለእስራኤል ቤት ከእንግዲህ ስለማልራራላቸው፣ ስሟን ሎሩሃማብለህ ጥራት።

7 ነገር ግን ለይሁዳ ቤት እራራለሁ፤ በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በጦርነት ወይም በፈረሶችና በፈረሰኞች ሳይሆን በአምላካቸውበእግዚአብሔርአድናቸዋለሁ።”

8 ጎሜር፣ ሎሩሃማን ጡት ካስጣለች በኋላ ሌላ ወንድ ልጅ ወለደች።

9 እግዚአብሔርምእንዲህ አለው፤ “ሎዓሚብለህ ጥራው፤ ምክንያቱም እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም፤ እኔም አምላካችሁ አይደለሁምና።

10 “ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ሊሰፈርና ሊቈጠር እንደማይችል እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናሉ፤ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ በተባሉበት ቦታ፣ ‘የሕያው አምላክ ልጆች’ ተብለው ይጠራሉ።

11 የይሁዳ ሕዝብና የእስራኤል ሕዝብ እንደ ገና አንድ ይሆናሉ አንድ መሪም ይሾማሉ፤ አንድ ሆነውም በምድሪቱ ይገናሉ፤ የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *