1 እስራኤል የተንዠረገገ ወይን ነበር፤
ብዙ ፍሬም አፈራ፤
ፍሬው በበዛ መጠን፣
ብዙ መሠዊያዎችን ሠራ፤
ምድሩ በበለጸገ መጠን፣
የጣዖታት ማምለኪያ ዐምዶችን አስጌጠ።
2 ልባቸው አታላይ ነው፤
ስለዚህም በደላቸውን ይሸከማሉ።
እግዚአብሔርመሠዊያዎቻቸውን ያወድማል፤
የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ያፈራርሳል።
3 እነርሱም፣ “እኛ ንጉሥ የለንም፤
እግዚአብሔርንአላከበርንምና፤
ንጉሥ ቢኖረንስ፣
ምን ሊያደርግልን ይችል ነበር?” ይላሉ።
4 ከንቱ ተስፋ ይሰጣሉ፤
በሐሰት በመማል፣
ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤
ስለዚህም ፍርድ፣
በዕርሻ ውስጥ እንደሚገኝ መርዛማ ዐረም ይበቅላል።
5 በሰማርያ የሚኖረው ሕዝብ፣
በቤትአዌን ስላለው የጥጃ ጣዖት ይፈራል፤
ሕዝቡም ያለቅስለታል፤
በክብሩ እጅግ ደስ ያላቸው ሁሉ፣
አመንዝራ ካህናትም እንደዚሁ ያለቅሱለታል፤
በምርኮ ከእነርሱ ተወስዶአልና።
6 ለታላቁ ንጉሥ እንደ እጅ መንሻ፣
ወደ አሦር ይወሰዳል፤
ኤፍሬም ይዋረዳል፤
እስራኤልም ስለ ጣዖቱ ያፍራል።
7 ሰማርያና ንጉሥዋ፣
በውሃ ላይ እንዳለ ኩበት ተንሳፍፈው ይጠፋሉ።
8 የእስራኤል ኀጢአት የሆነው፣
የአዌን ማምለኪያ ኰረብታ ይጠፋል፤
እሾኽና አሜኬላ ይበቅልባቸዋል፤
መሠዊያዎቻቸውንም ይወርሳል፤
በዚያን ጊዜ ተራሮችን፣ “ሸፍኑን!”
ኰረብታዎችንም፣ “ውደቁብን!” ይላሉ።
9 “እስራኤል ሆይ፤ ከጊብዓ ጊዜ ጀምሮ ኀጢአት ሠራችሁ፤
በዚያም ጸናችሁ፤
በጊብዓ የነበሩትን ክፉ አድራጊዎች፣
ጦርነት አልጨረሳቸውምን?
10 በፈለግሁ ጊዜ እቀጣቸዋለሁ፤
ስለ ድርብ ኀጢአታችሁም ይቀጧቸው ዘንድ፣
በእነርሱ ላይ ይሰበሰባሉ፤
11 ኤፍሬም ማበራየት እንደምትወድ፣
እንደ ተገራች ጊደር ነው፤
በተዋበ ጫንቃዋም ላይ፣
ቀንበርን አኖራለሁ፤
ኤፍሬምን እጠምዳለሁ፤
ይሁዳ ያርሳል፤
ያዕቆብም መሬቱን ያለሰልሳል።
12 ለራሳችሁ ጽድቅን ዝሩ፤
የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ዕጨዱ፤
ዕዳሪውንም መሬት ዕረሱ፤
እርሱም መጥቶ፣
ጽድቅን በላያችሁ እስኪያዘንብ ድረስ፣
እግዚአብሔርንየምትፈልጉበት ጊዜ ነውና።
13 እናንተ ግን ክፋትን ዘራችሁ፤
ኀጢአትንም ዐጨዳችሁ፤
የሐሰትንም ፍሬ በላችሁ።
በራሳችሁ ጒልበት፣
በተዋጊዎቻችሁም ብዛት ታምናችኋልና፣
14 ሰልማን፣ ቤትአርብኤልን በጦርነት ጊዜ እንዳፈራረሰ፣
እናቶችንም ከልጆቻቸው ጋር በምድር ላይ እንደ ፈጠፈጣቸው፣
ሽብር በሕዝብህ ላይ ይመጣል፤
ምሽጎችህም ሁሉ ይፈራርሳሉ፤
15 ስለዚህ ቤቴል ሆይ፤ ክፋትሽ ታላቅ ስለ ሆነ፣
በአንቺም ላይ እንደዚሁ ይሆናል፤
ያ ቀን ሲደርስም፣
የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል።