በረከትን ለማግኘት ንስሓ መግባት
1 እስራኤል ሆይ፤ በኀጢአትህ ምክንያት ስለ ወደቅህ፣
ወደ አምላክህ ወደእግዚአብሔርተመለስ።
2 የምትሉትን ቃል ይዛችሁ፣
ወደእግዚአብሔርተመለሱ፤
እንዲህም በሉት፤
“ኀጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤
የከንፈራችንንም ፍሬ እንድናቀርብ፣
በምሕረትህ ተቀበለን።
3 አሦር ሊያድነን አይችልም፤
በጦር ፈረሶችም ላይ አንቀመጥም፤
ከእንግዲህም የገዛ እጆቻችን የሠሯቸውን፣
‘አምላኮቻችን’ አንላቸውም፤
ድኻ አደጉ ከአንተ ርኅራኄ ያገኛልና።”
4 “እኔ ከዳተኛነታቸውን እፈውሳለሁ፤
እንዲሁ እወዳቸዋለሁ፤
ቊጣዬ ከእነርሱ ተመልሶአልና።
5 እኔ ለእስራኤል እንደ ጠል እሆናለሁ፤
እንደ ውብ አበባ ያብባል፤
እንደ ሊባኖስ ዝግባም፣
ሥር ይሰዳል፤
6 ቅርንጫፉ ያድጋል፤
ውበቱ እንደ ወይራ ዛፍ፣
ሽታውም እንደ ሊባኖስ ዝግባ ይሆናል።
7 ሰዎች እንደ ገና ከጥላው በታች ያርፋሉ፤
እርሱም እንደ እህል ይለመልማል፤
እንደ ወይን ተክል ያብባል፤
ዝናውም እንደ ሊባኖስ የወይን ጠጅ ይወጣል።
8 ኤፍሬም ሆይ፤ ከእንግዲህ ከጣዖት ጋር
ምን ጒዳይ አለኝ?
የምሰማህና የምጠነቀቅልህ እኔ ነኝ፤
እኔ እንደለመለመ የጥድ ዛፍ ነኝ፤
ፍሬያማነትህም ከእኔ የተነሣ ነው።”
9 ጥበበኛ የሆነ እነዚህን ነገሮች ያስተውላል፤
አስተዋይም እነዚህን ነገሮች ይረዳል።
የእግዚአብሔርመንገድ ቅን ነውና፤
ጻድቃን ይሄዱበታል፤
ዐመፀኞች ግን ይሰናከሉበታል።