ሆሴዕ 9

በእስራኤል ላይ የሚደርሰው ቅጣት

1 እስራኤል ሆይ፤ ደስ አይበልሽ፤

እንደ ሌሎችም ሕዝቦች ሐሤት አታድርጊ፤

ለአምላክሽ ታማኝ አልሆንሽምና፤

በየእህል ዐውድማውም ላይ፣

ለጋለሞታ የሚከፈለውን ዋጋ ወደሻል።

2 የእህል አውድማዎችና የወይን መጭመቂያዎች ሕዝቡን አይመግቡም፤

አዲሱም የወይን ጠጅ ይጐድልባቸዋል።

3 በእግዚአብሔርምድር አይቀመጡም፤

ኤፍሬም ወደ ግብፅ ይመለሳል፤

የረከሰውንም ምግብበአሦር ይበላል።

4 የወይን ጠጅን ቍርባንለእግዚአብሔርአያፈሱም፤

መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፤

እንዲህ ዐይነቱ መሥዋዕት ለእነርሱ የሐዘንተኞች እንጀራ ይሆንባቸዋል፤

የሚበሉትም ሁሉ ይረክሳሉ።

ይህ ምግብ ለገዛ ራሳቸው ይሆናል፤

ወደእግዚአብሔርምቤተ መቅደስ አይገባም።

5 በእግዚአብሔርየበዓል ቀናት፣

በዓመት በዓሎቻችሁም ቀን ምን ታደርጋላችሁ?

6 ከጥፋት ቢያመልጡም እንኳ፣

ግብፅ ትሰበስባቸዋለች፤

ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች።

የብር ሀብታቸውን ዳዋ ያለብሰዋል፤

ድንኳኖቻቸውም እሾኽ ይወርሰዋል።

7 የቅጣት ቀን መጥቶአል፤

የፍርድም ቀን ቀርቦአል፤

እስራኤልም ይህን ይወቅ!

ኀጢአታችሁ ብዙ፣

ጠላትነታችሁም ታላቅ ስለ ሆነ፣

ነቢዩ እንደ ሞኝ፣

መንፈሳዊውም ሰው እንደ እብድ ተቈጥሮአል።

8 ነቢዩ ከአምላኬ ጋር ሆኖ፣

የኤፍሬም ጠባቂ ነው፤

ዳሩ ግን በመንገዱ ሁሉ ወጥመድ፣

በአምላኩም ቤት ጠላትነት ይጠብቀዋል።

9 በጊብዓ እንደ ነበረው፣

በርኵሰት ውስጥ ተዘፍቀዋል፤

እግዚአብሔር ክፋታቸውን ያስባል፤

ስለ ኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።

10 “እስራኤልን ማግኘቴ፣

የወይንን ፍሬ፣ በምድረ በዳ የማግኘት ያህል ነበር፤

አባቶቻችሁንም ማየቴ፣

የመጀመሪያውን የበለስ ፍሬ የማየት ያህል ነበር፤

ወደ ብዔልፌጎር በመጡ ጊዜ ግን፣

ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ራሳቸውን ለዩ፤

እንደ ወደዱትም ጣዖት የረከሱ ሆኑ።

11 የኤፍሬም ክብር እንደ ወፍ በሮ ይጠፋል፤

መውለድ፣ ማርገዝና መፀነስ የለም።

12 ልጆችን ቢያሳድጉ እንኳ፣

ልጅ አልባ እስኪሆኑ ድረስ እነጥቃቸዋለሁ፤

ፊቴን ከእነርሱ በመለስሁ ጊዜ፣

ወዮ ለእነርሱ

13 ኤፍሬምን እንደ ጢሮስ፣

በመልካም ስፍራ ተተክሎ አየሁት፤

አሁን ግን ኤፍሬም ልጆቹን፣

ለነፍሰ ገዳዮች አሳልፎ ይሰጣል።”

14 እግዚአብሔርሆይ፤ ስጣቸው፤

ምን ትሰጣቸዋለህ?

የሚጨነግፉ ማሕፀኖችን፣

የደረቁ ጡቶችን ስጣቸው።

15 “በጌልገላ ካደረጉት ክፋታቸው ሁሉ የተነሣ፣

እኔ በዚያ ጠላኋቸው፤

ስለሠሩት ኀጢአት፣

ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፤

ከእንግዲህም አልወዳቸውም፤

መሪዎቻቸው ሁሉ ዐመፀኞች ናቸው።

16 ኤፍሬም ተመታ፤

ሥራቸው ደረቀ፤

ፍሬም አያፈሩም፤

ልጆች ቢወልዱም እንኳ፣

ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን እገድላለሁ።”

17 ባለመታዘዛቸው ምክንያት፣

አምላኬ ይጥላቸዋል፤

በአሕዛብም መካከል ተንከራታች ይሆናሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *