በእስራኤል መሪዎች ላይ የተላለፈ ፍርድ
1 መንፈስም ወደ ላይ አነሣኝ፤ ከዚያም በምሥራቅ በኩል ወዳለው ወደእግዚአብሔርቤት በር አመጣኝ። በበሩም መግቢያ ላይ ሃያ አምስት ሰዎች ነበሩ፤ በእነርሱም መካከል የሕዝቡን መሪዎች የዓዙርን ልጅ ያእዛንያንና የበናያስን ልጅ ፈላጥያንን አየሁ።
2 እግዚአብሔርምእንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ክፋትን የሚያቅዱና በዚህችም ከተማ ላይ ተንኰልን የሚመክሩ ናቸው።
3 እነርሱም፣ “ቤቶች የሚሠሩበት ጊዜ ቅርብ አይደለምን?ይህች ከተማ ድስት ናት፤ እኛም ሥጋ ነን’ ብለዋል።
4 ስለዚህ ትንቢት ተናገርባቸው፤ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር።”
5 የእግዚአብሔርምመንፈስ በላዬ ወረደ እንዲህም አለኝ፤ “እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እናንተ እንዲህ ብላችኋል፤ እኔ ግን የልባችሁን ሐሳብ ዐውቃለሁ።
6 በዚህች ከተማ ብዙ ሰው ገድላችኋል፤ መንገዶቿንም ሬሳ በሬሳ አድርጋችኋል።’
7 “ስለዚህ ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘በዚያ የጣላችኋቸው ሬሳዎች እነርሱ ሥጋ ናቸው፤ ይህችም ከተማ ድስት ናት፤ እናንተን ግን ከውስጧ አወጣችኋለሁ።
8 ሰይፍን ፈርታችኋል፤ እኔም ሰይፍ እልክባችኋለሁ፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።
9 ከከተማዪቱ አውጥቼ ለባዕዳን አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ ፍርድንም አመጣባችኋለሁ።
10 በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ በእስራኤል ድንበር ላይ እፈርድባችኋለሁ፤ በዚያ ጊዜም እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
11 ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም፤ እናንተም በውስጧ ሥጋ አትሆኑም፤ በእስራኤልም ድንበር ላይ እፈርድባችኋለሁ፤
12 በዚያ ጊዜ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እናንተ በዙሪያችሁ ያሉትን አሕዛብ ሥርዐት ተከተላችሁ እንጂ ትእዛዜን አልፈጸማችሁም ሕጌንም አልጠበቃችሁምና።”
13 ትንቢት እየተናገርሁ ሳለ፣ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፤ እኔም በግንባሬ ተደፍቼ፣ “ጌታእግዚአብሔርሆይ፣ ወዮ! የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽመህ ታጠፋለህን?” በማለት በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ።
14 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
15 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ወንድሞችህ፣ የራስህ ዘመዶችናየእስራኤል ቤት ሁሉ፤ ‘ከእግዚአብሔርርቀዋል፤ ይህች ምድር ርስት ሆና ለኛ ተሰጥታናለች’ ብለው የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የተናገሩባቸው ናቸው።
የእስራኤል የመመለስ ተስፋ
16 “ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘በአሕዛብ መካከል ብሰድዳቸውም፤ በአገሮች መካከል ብበታትናቸውም፣ በሄዱባቸው አገሮች ሁሉ ለጥቂት ጊዜ መቅደስ ሆኜአቸዋለሁ’ ”።
17 “ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ከአሕዛብ መካከል እሰበስባችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባቸው አገሮች እመልሳችኋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እንደ ገና እሰጣችኋለሁ።”
18 “ወደዚያ በተመለሱ ጊዜ የረከሱ ምስሎቿንና ጸያፍ ተግባሯን ያስወግዳሉ።
19 የማያወላውል ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ አዲስ መንፈስ በውስጣቸው አኖራለሁ፤ ድንጋዩን ልብ ከውስጣቸው አወጣለሁ፤ ሥጋ ልብም እሰጣቸዋለሁ።
20 ስለዚህ ትእዛዜን ይፈጽማሉ፤ ሕጌን ይጠብቃሉ። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።
21 ነገር ግን ልባቸው ወደ ረከሱ ምስሎቻቸውና ወደ ጸያፍ ተግባራቸው ያዘነበለውን እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።”
22 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፤ መንኰራኵሮቹም በአጠገባቸው ነበሩ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበር።
23 የእግዚአብሔርምክብር ከከተማዪቱ ውስጥ ተነሥቶ ወጣ፤ ከከተማዪቱም በስተ ምሥራቅ ካለው ተራራ በላይ ቆም አለ።
24 መንፈስም ወደ ላይ አነሣኝ፤ በእግዚአብሔርም መንፈስ በተሰጠው ራእይም በባቢሎንምድር ወደ ነበሩት ምርኮኞች አመጣኝ።
ከዚያም ያየሁት ራእይ ከእኔ ወጥቶ ሄደ፤
25 እኔምእግዚአብሔርያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞቹ ተናገርሁ።