ሕዝቅኤል 12

ምርኮው በትእምርት መቅረቡ

1 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ በዐመፀኛ ሕዝብ መካከል ተቀምጠሃል፤ የሚያዩበት ዐይን አላቸው፤ ነገር ግን አያዩም፤ የሚሰሙበትም ጆሮ አላቸው፤ ነገር ግን አይሰሙም፤ ዐመፀኛ ሕዝብ ናቸውና።

3 “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ እነርሱ እያዩህ በቀን ጓዝህን ጠቅልለህ ለመሰደድ ተዘጋጅ፤ ካለህበትም ስፍራ ተነሥተህ ወደ ሌላ ቦታ ሂድ፤ ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም ምናልባት ይህን ያስተውሉታል።

4 በቀን እያዩ ጓዝህን እንደ ስደተኛ ጓዝ አውጣው፤ በምሽትም እያዩህ ስደተኛ እንደሚወጣ ውጣ።

5 እነርሱ እያዩ ግንቡን ነድለህ ጓዝህን በዚያ አሹልክ።

6 በፊታቸው ጓዝህን በትከሻህ ላይ አስቀምጥ፣ በምሽትም ተሸክመህ ውጣ። ለእስራኤል ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና ምድሪቱን እንዳታይ ፊትህን ሸፍን።”

7 እኔም በታዘዝሁት መሠረት አደረግሁ፤ በቀን ጓዜን ጠቅልዬ እንደ ስደተኛ ጓዝ አወጣሁ፤ በምሽትም ግንቡን በእጄ ነደልሁት፤ እያዩኝም በምሽት ጓዜን በትከሻዬ ላይ ተሸክሜ አወጣሁ።

8 በማግስቱም ጠዋትየእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

9 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ዐመፀኛው የእስራኤል ቤት፣ ‘ይህ የምታደርገው ምንድን ነው?’ ብለው ጠይቀውህ አልነበረምን?”

10 “እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ለሚኖረው መስፍንና በዚያ ለሚገኙት ለእስራኤል ቤት ሁሉ ነው’ ”።

11 ‘እኔ ምልክታችሁ ነኝ’ በላቸው።

“እኔ እንዳደረግሁት፤ እንዲሁ በእነርሱ ይደረግባቸዋል፤ በምርኮኛነትም ተሰደው ይሄዳሉ።

12 “በመካከላቸው ያለው መስፍን በምሽት ጓዙን በትከሻው ተሸክሞ ይወጣል፤ ሾልኮ እንዲሄድ ግንቡ ይነደልለታል፤ ምድሪቱንም እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል።

13 መረቤን በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ በወጥመዴም ይያዛል፤ ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ነገር ግን እርሷን ሳያያት በዚያ ይሞታል።

14 በዙሪያው ያሉትን ረዳቶቹንና ወታደሮቹን ሁሉ ወደ ነፋስ እበትናቸዋለሁ፤ በተመዘዘም ሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ።

15 “በአሕዛብ መካከል ስበትናቸውና በአገሮችም መካከል ስዘራቸው፤ በዚያን ጊዜ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ያውቃሉ።

16 ነገር ግን በሄዱባቸው አሕዛብ መካከል ስለ ጸያፍ ተግባራቸው ይናገሩ ዘንድ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ከሰይፍ ከራብና ከቸነፈር አተርፋለሁ። በዚያን ጊዜ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ያውቃሉ።”

17 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

18 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ምግብህን በድንጋጤ ብላ፤ ውሃህንም በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ጠጣ።

19 ለምድሪቱ ሕዝብ እንዲህ በል፤ ‘ጌታእግዚአብሔርበኢየሩሳሌምና በእስራኤል ምድር ስለሚኖሩት እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ዐመፅ የተነሣ ምድራቸው ስለምትራቈት፣ ምግባቸውን በጭንቀት ይመገባሉ፤ ውሃቸውንም በፍርሀት ይጠጣሉ።

20 ሰው ይኖርባቸው የነበሩ ከተሞች ባድማ ይሆናሉ፤ ምድሪቱም ወና ትሆናለች። በዚያ ጊዜ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”

21 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

22 “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል ምድር፣ ‘ዘመኑ ረዝሞአል፤ ራእዩ ሁሉ ከንቱ ሆኖአል’ የምትሉት ይህ አባባል ምንድ ነው?

23 እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ይህን አባባል እሽራለሁ፤ በእስራኤልም ምድር ዳግመኛ በንግግራቸው አይጠቀሙበትም”። እንዲህም በላቸው፤ “ራእዩ ሁሉ የሚፈጸምበት ጊዜ ቀርቦአል፤

24 በእስራኤል ሕዝብ መካከል ከእንግዲህ ሐሰተኛ ራእይና አሳሳች ሟርት አይገኝምና።

25 ነገር ግን እኔእግዚአብሔርእናገራለሁ፤ የምናገረውም ቃል ሳይዘገይ ይፈጸማል፤ እናንተ ዐመፀኛ ቤት ሆይ፤ የተናገርሁትን ሁሉ በዘመናችሁ እፈጽማለሁ” ይላል ጌታእግዚአብሔር።’ ”

26 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

27 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት፣ ‘ይህ ሰው የሚያየው ራእይ ገና ለሩቅ ዘመን የሚሆን ነው፤ የሚናገረውም ትንቢት የረጅም ጊዜ ትንቢት ነው’ ይላሉ።

28 “ስለዚህ እንዲህ በላቸው፣ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘ከተናገርሁት ቃል ከእንግዲህ የሚዘገይ የለም፤ የምለው ሁሉ ይፈጸማል” ይላል ጌታእግዚአብሔር።’ ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *