ባዕድ አምልኮ ተከታዮች መወገዛቸው
1 ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ።
2 የእግዚአብሔርምቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
3 “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል፤ ክፋታቸውን እንደ ማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፤ ታዲያ ከእኔ እንዳች ነገር እንዲጠይቁ ልፍቀድላቸውን?
4 ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ማንኛውም እስራኤላዊ ጣዖትን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ አድርጎ በፊቱ በማስቀመጥ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔእግዚአብሔርእንደ ጣዖቱ ብዛት እመልስለታለሁ።
5 በጣዖቶቻቸው ምክንያት ከእኔ የተለዩትን የእስራኤልን ቤት ሁሉ ልብ ወደ ራሴ ለመመለስ ይህን አደርጋለሁ።’
6 “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ንስሓ ግቡ ከጣዖቶቻችሁ ተመለሱ፤ ጸያፍ ተግባራችሁንም ሁሉ ተዉ።”
7 “ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ራሱን ከእኔ በመለየት ጣዖቶችን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ በማድረግ በፊቱ አስቀምጦ ከእኔ ለመጠየቅ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ ራሴእግዚአብሔርእመልስለታለሁ።
8 ፊቴን በክፋት ወደዚያ ሰው እመልሳለሁ፤ መቀጣጫና መተረቻ አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
9 “ ‘ነቢዩ ትንቢት ይናገር ዘንድ ቢታለል፣ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔእግዚአብሔርነኝ፤ ክንዴን በእርሱ ላይ አነሣለሁ፤ ከሕዝቤ ከእስራኤል መካከልም አጠፋዋለሁ።
10 በደላቸው በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ነቢዩም እርሱን ሊጠይቀው ከመጣው ሰው ጋር እኩል በደለኛ ይሆናል።
11 ከእንግዲህ የእስራኤል ሕዝብ መንገድ ስቶ ከእኔ አይለይም፤ ተመልሶም በኀጢአቱ ሁሉ ራሱን አያረክስም። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
የማያመልጡት ፍርድ
12 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
13 “የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ አገር በእኔ ባለመታመን ቢበድለኝና እኔም እጄን በላዩ ዘርግቼ የምግብ ምንጩን ባደርቅ፣ ራብንም አምጥቼበት ሰውንና እንስሳቱን ብገድል፣
14 ኖኅ፣ ዳንኤልናኢዮብ እነዚህ ሦስቱ በዚያ ቢኖሩ እንኳ፣ በጽድቃቸው የሚያድኑት ራሳቸውን ብቻ ነው፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።
15 “የዱር አራዊትንም በአገሪቱ ላይ ሰድጄ አገሪቱን ሕፃናት አልባ ቢያደርጓትና ከአራዊቱም የተነሣ ምድሪቱ ሰው እስከማያልፍባት ባድማ ብትሆን፣
16 ‘በሕያውነቴ እምላለሁ!’ ይላል ጌታእግዚአብሔር፤ እነዚህ ሦስቱ ሰዎች ቢኖሩባት እንኳ፣ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም፤ እነርሱ ብቻ ይድናሉ፤ ምድሪቱ ግን ባድማ ትሆናለች።’
17 “ሰይፍን በአገሪቱ ላይ አምጥቼ፣ ‘ሰይፍ በዚህ ምድር ይለፍ’ ብል፣ ሰውንና እንስሳን ባጠፋ፣
18 በሕያውነቴ እምላለሁ ይላልእግዚአብሔር፤ እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባትም እንኳ ራሳቸው ብቻ ይድናሉ እንጂ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም።
19 “ቸነፈርንም በምድሪቱ ላይ ብሰድና ደም በማፍሰስ መዓቴን አውርጄ ሰውንና እንስሳን ባጠፋ፣
20 በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ ቢኖሩባትም እንኳ በጽድቃቸው ራሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችን ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም።
21 “ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላልና፤ ‘ሰውንና እንስሳቱን ለማጥፋት አራቱን አስፈሪ ፍርዶቼን፦ ሰይፍን፣ ራብን፣ የዱር አራዊትንና ቸነፈርን በኢየሩሳሌም ላይ በማመጣበት ጊዜ ምንኛ የከፋ ይሆን!
22 ነገር ግን ከዚያ ወጥተው የሚተርፉ ወንዶችና ሴቶች ልጆች አሉ፤ እነርሱም ወደ እናንተ ይመጣሉ፤ እናንተም አካሄዳቸውንና ተግባራቸውን በምታዩበት ጊዜ በኢየሩሳሌም ላይ ስላመጣሁት መከራ፣ ስላደረስሁባትም አስከፊ ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ።
23 አካሄዳቸውንና ተግባራቸውን በምታዩበት ጊዜ፣ ትጽናናላችሁ፤ አንዳች ነገር በከንቱ እንዳላደረገሁ ትረዳላችሁና፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።’ ”