ሕዝቅኤል 2

የሕዝቅኤል መጠራት

1 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ተነሥተህ በእግርህ ቁም፤ እኔም እናገርሃለሁ” አለኝ።

2 እርሱም ሲናገር፣ መንፈስ ወደ ውስጤ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ ሲናገረኝም ሰማሁት።

3 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእኔ ላይ ወደ ዐመፀው ወደ ዐመፀኛው የእስራኤል ሕዝብ እልክሃለሁ፤ እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐምፀውብኛል።

4 ሕዝቡም እልኸኛና ዐንገተ ደንዳና ነው፤ እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል’ በላቸው።

5 እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለሆኑ፤ ቢሰሙም ባይሰሙም በመካከላቸው ነቢይ እንደነበር ያውቃሉ።

6 አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ እነርሱን ወይም ቃላቸውን አትፍራ፤ ኵርንችትና እሾኽ በዙሪያህ ቢኖሩም፣ በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም አትፍራ። እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም፣ አንተ በሚሉህ ነገር አትፍራ፤ እነርሱም አያስደንግጡህ።

7 እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለሆኑ፣ ቢሰሙም ባይሰሙም አንተ ቃሌን ንገራቸው።

8 አንተ ግን የሰው ልጅ ሆይ፤ እኔ የምልህን ስማ፤ እንደዚያ ዐመፀኛ ቤት ዐታምፅ፤ አፍህን ክፈት፤ የምሰጥህንም ብላ።”

9 ከዚህም በኋላ፣ እነሆ አንድ እጅ ወደ እኔ ተዘርግቶ አየሁ፤ ጥቅልል መጽሐፍም ነበረበት፤

10 እርሱም በፊቴ ዘረጋው፤ መጽሐፉም ከፊትና ከኋላው የሰቈቃ፣ የልቅሶና የዋይታ ቃላት ተጽፎበት ነበር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *