ሕዝቅኤል 21

የቅጣት በትር የሆነችው ባቢሎን

1 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አዙር፤ በመቅደሱ ላይ ቃል ተናገር፤ በእስራኤል ምድር ላይ ትንቢት ተንብይ፤

3 እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ እኔ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ሰይፌን ከሰገባው እመዛለሁ፤ ጻድቁንም፣ ክፉውንም ከአንተ ዘንድ አስወግዳለሁ።

4 ጻድቁንም ክፉውንም ስለማስወ ግድ ሰይፌ ከደቡብ ጀምሮ እስከ ሰሜን ባለው ሕዝብ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል።

5 ሰይፌን ከሰገባው የመዘዝሁት እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ሕዝቡ ሁሉ ያውቃል፤ እርሱም ወደ ሰገባው አይመለስም።’

6 “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ አቃስት፤ በተሰበረ ልብና በመረረ ሐዘን አቃስት፤

7 እነርሱም፣ ‘ለምን ታቃስታለህ?’ ቢሉህ፣ “ስለሚመጣው ክፉ ወሬ ነው፤ ልብ ሁሉ ይቀልጣል፤ እጅም ሁሉ ይዝላል፤ ነፍስ ሁሉ ይደክማል፤ ጒልበትም ሁሉ ውሃ ይሆናል’ በላቸው። እነሆ ይመጣል፤ ይፈጸማልም፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።”

8 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

9 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“ሰይፍ! ሰይፍ!

የተሳለ የተወለወለም፤

10 የተሳለው ሊገድል፣

የተወለወለውም እንደ መብረቅ ሊብረቀረቅ ነው!

“ ‘ታዲያ፣ እንዴት ደስ ሊለን ይችላል? ሰይፉ የልጄን በትረ መንግሥት እንደ ማንኛውም በትር ንቆአል።

11 “ ‘በእጁ እንዲያዝ፣

ሰይፉ ሊወለወል ተሰጥቶአል፤

ገዳዩ በእጁ እንዲጨብጠው፣

ተስሎአል፤ ተወልውሎአል።

12 የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ በሕዝቤ ላይ፣

በእስራኤልም መሳፍንት ሁሉ ላይ መጥቶአልና፤

ጩኸት፣ ዋይታም አሰማ።

እነርሱ ከሕዝቤ ጋር በአንድ ላይ፣

ለሰይፍ ተጥለዋል፤

ስለዚህ ደረትህን ምታ።

13 “ ‘ፈተና በእርግጥ ይመጣል፤ ሰይፉ የናቀው በትረ መንግሥት ዘላቂነት ባይኖረውስ? ይላል ጌታእግዚአብሔር።’

14 “እንግዲህ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤

በእጅህም አጨብጭብ፤

ሰይፉ ሁለት ጊዜ፣

ሦስት ጊዜም ይምታ፤

በእጅጉ የሚገድል፣

ለግድያ የሚሆን፣

በየአቅጣጫውም የሚከባቸው ሰይፍ ነው።

15 ልብ ሁሉ ይቀልጥ ዘንድ፣

የሚወድቁትም እንዲበዙ፣

በበሮቻቸው ሁሉ፣

የግድያውን ሰይፍአኑሬአለሁ።

ወዮ! እንዲያብረቀርቅ ተወልውሎአል፤

ለመግደልም ተመዞአል።

16 ሰይፍ ሆይ፤ በስለትህ አቅጣጫ ሁሉ፣

ወደ ቀኝም፣

ወደ ግራም ቍረጥ።

17 እኔም በእጄ አጨበጭባለሁ፤

ቍጣዬም ይበርዳል፤

እኔእግዚአብሔርተናግሬአለሁ።”

18 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

19 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ የሚመጣባቸውን የሁለት መንገዶች ካርታ ንደፍ፤ መንገዶቹም ከአንድ አገር የሚነሡ ናቸው፤ መንገዱ ወደ ከተማው በሚገነጠልበት ቦታ ላይ ምልክት አቁም።

20 በአሞናውያን ከተማ በረባት ላይ ለሚመጣው ሰይፍ አንደኛውን መንገድ ምልክት አድርግ፤ በይሁዳና በተመሸገችው ከተማ በኢየሩሳሌም ላይ ለሚመጣውም ሰይፍ ሁለተኛውን መንገድ ምልክት አድርግ።

21 የባቢሎን ንጉሥ በጥንቈላ ምሪት ለማግኘት በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ ጐዳናዎች መጋጠሚያ ላይ ይቆማል፤ ቀስቶቹን በመወዝወዝ ዕጣ ይጥላል፤ አማልክቱን ያማክራል፤ ጒበትንም ይመረምራል።

22 የቅጥር መደርመሻ አምጥቶ እንዲያቆም፣ ለመግደል ትእዛዝ እንዲሰጥ፣ ፉከራ እንዲያሰማ፣ ቅጥር መደርመሻውን በከተሞች በር ላይ እንዲያደርግ፣ የዐፈር ድልድል እንዲያበጅና ምሽግ እንዲሠራ የኢየሩሳሌም ዕጣ በቀኝ እጁ ወጣ።

23 ይህም ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ለገቡት የተሳሳተ ምሪት ይመስላል፤ እርሱ ግን በደላቸውን ያሳስባቸዋል፤ ማርኮም ይዞአቸው ይሄዳል።

24 “ስለዚህ ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ በምታደርጉት ሁሉ ኀጢአታችሁን በመግለጽ፣ በግልጽም በማመፅ በደላችሁን ስላሳሰባችሁ፣ እንዲህም ስላደረጋችሁ በምርኮ ትወሰዳላችሁ።

25 “ ‘አንተ የግፍ ጽዋህ የሞላ፣ የምትቀጣበት ቀን የደረሰ፣ ርኩስና ክፉ የእስራኤል መስፍን ሆይ፤

26 ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ጥምጥምህን አውልቅ፤ ዘውድህን ጣል፤ እንደ ከዚህ በፊቱ አይሆንም፤ ዝቅ ያለው ከፍ ይላል፤ ከፍ ያለውም ዝቅ ይላል።

27 ባድማ! ባድማ! ባድማ አደርጋታለሁ፤ የሚገባው ባለ መብት እስከሚመጣ ድረስ እንደ ቀድሞው አትሆንም፤ ለእርሱም ደግሞ እሰጣታለሁ።” ’

28 “አንተ የሰው ልጅ ሆይ! እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ስለ አሞናውያንና ስለ ስድባቸው ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“ ‘ሰይፍ! ሰይፍ!

ሊገድል የተመዘዘ፣

ሊያጠፋ የተጠረገ፣

እንደ መብረቅ ሊያብረቀርቅ የተወለወለ፤

29 የታለመልህ የሐሰት ራእይ፣

የተነገረልህ የውሸት ሟርት ቢኖርም፣

የግፍ ጽዋቸው በሞላ፣

ቀናቸው በደረሰ፣

መታረድ በሚገባቸው ክፉዎች፣

አንገት ላይ ይሆናል።

30 ሰይፉን ወደ ሰገባው መልሰው፤

በተፈጠርህበት ምድር፣

በተወለድህበትም አገር፣

በዚያ እፈርድብሃለሁ።

31 መዓቴን በላይህ አፈሳለሁ፤

የቍጣዬንም እሳት አነድብሃለሁ፣

በጥፋት ለተካኑ፣

ለጨካኞች ሰዎች አሳልፌ እሰጥሃለሁ።

32 ለእሳት ማገዶ ትሆናለህ፣

ደምህ በምድርህ ይፈሳል፣

ከእንግዲህ መታሰቢያ አይኖርህም፤

እኔእግዚአብሔርተናግሬአለሁና።’ ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *