ሕዝቅኤል 24

የድስቱ ምሳሌ

1 በዘጠነኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐሥረኛው ቀንየእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን ቀን፣ የዛሬውን ዕለት ለይተህ መዝግብ፤ የባቢሎን ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በዚህ ቀን ከቦአታልና።

3 ለዚህ ዐመፀኛ ቤት እንዲህ ብለህ ተምሳሌት ተናገር፤ ‘ልዑልእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“ ‘ብረት ድስት በእሳት ላይ ጣድ፤

ከጣድህም በኋላ ውሃ ጨምርበት።

4 ሙዳ፣ ሙዳ ሥጋ፣

ምርጥ ምርጡን ቍርጥ ሁሉ፣ ጭንና ወርቹን ጨምርበት፤

የተመረጡ ዐጥንቶችንም ሙላበት።

5 ከመንጋው ሙክቱን ውሰድ፤

ዐጥንቱን ለማብሰል ብዙ ማገዶ ከሥሩ ጨምር፤

ሙክክ እስከሚል ቀቅለው፤

ዐጥንቱም ይብሰል።

6 “ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላልና፤

“ ‘ለዛገችው ብረት ድስት

ዝገቷም ለማይለቅ፣

ደም ላፈሰሰችው ከተማ ወዮላት!

መለያ ዕጣ ሳትጥል

አንድ በአንድ አውጥተህ ባዶ አድርገው።

7 “ ‘የሰው ደም በመካከሏ አለ፤

በገላጣ ዐለት ላይ አደረገችው እንጂ፣

ዐፈር ሊሸፍነው በሚችል፣

በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም።

8 ቍጣዬ እንዲነድና ለመበቀል እንዲያመቸኝ፣

ይሸፈንም ዘንድ እንዳይችል፣

ደሟን በገላጣ ዐለት ላይ አፈሰስሁ።

9 “ ‘ስለዚህ ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“ ‘ደም ላፈሰሰችው ከተማ ወዮላት!

እኔም ደግሞ የምትቃጠልበትን ማገዶ እቈልላለሁ።

10 ማገዶውን ከምርበት፤

እሳቱን አንድድ፤

ቅመም ጨምረህበት፣

ሥጋውን በሚገባ ቀቅል፤

ዐጥንቱም ይረር።

11 ጒድፉ እንዲቀልጥ፣

ዝገቱም በእሳት እንዲበላ፣

ባዶው ድስት እስኪሞቅ፣

መደቡም እስኪግል ከሰል ላይ ጣደው።

12 ብዙ ጒልበት ቢፈስበትም፣

የዝገቱ ክምር፣

በእሳት እንኳ፣ ሊለቅ አልቻለም።

13 “ ‘የረከስሽው በብልግናሽ ነው፤ ቍጣዬ በአንቺ ላይ እስኪፈጸም ድረስ ከእንግዲህ ንጹሕ አትሆኚም፤ ከርኵሰትሽ ላነጻሽ ፈልጌ፣ መንጻት አልወደድሽምና።

14 “ ‘እኔእግዚአብሔርተናግሬአለሁ፤ የምሠራበትም ጊዜ ደርሶአል፤ ወደ ኋላ አልልም፤ አልራራም፤ አላመነታምም። እንደ መንገድሽና እንደ ተግባርሽ ይፈረድብሻል፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።’ ”

የሕዝቅኤል ሚስት መሞት

15 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

16 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የዐይንህ ማረፊያ የሆነውን ነገር በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተ ግን ዋይታ አታሰማ፤ አታልቅስ፤ እንባህንም አታፍስስ፤

17 ድምፅህን ዝቅ አድርገህ በሐዘን አንጐራጒር እንጂ ለሞተው አታልቅስ። ጥምጥምህን ከራስህ አታውርድ፤ ጫማህንም አታውልቅ፤ አፍህ ድረስ አትሸፋፈን፤ የዕዝን እንጀራም አትብላ።”

18 እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፤ ሚስቴም ማታውኑ ሞተች፤ በማግሥቱም ጠዋት እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።

19 ሕዝቡም፣ “ይህን ስታደርግ ለእኛ የምታስተላልፈው መልእክት ምን እንደሆነ አትነግረንምን?” አሉኝ።

20 እኔም እንዲህ አልኋቸው፤ “የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

21 ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “የኀይላችሁን ትምክሕት፣ የዐይናችሁ ማረፊያና የልባችሁ ደስታ የሆነውን መቅደሴን አረክሳለሁ። ትታችኋቸው የሄዳችሁ ወንድና ሴት ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።

22 እኔ እንዳደረግሁም ታደርጋላችሁ፤ አፋችሁ ድረስ አትሸፋፈኑም፤ የዕዝን እንጀራም አትበሉም፤

23 ጥምጥማችሁን ከራሳችሁ አታወርዱም፤ ጫማችሁንም አታወልቁም። በኀጢአታችሁ ትመነምናላችሁ፤ እርስ በርስ ታቃስታላችሁ እንጂ ሐዘን አትቀመጡም፤ አታለቅሱምም።

24 ሕዝቅኤል ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ እንዳደረገው ታደርጋላችሁ፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ እኔ ጌታእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”

25 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፤ ኀይላቸውን፣ ደስታቸውንና፣ ክብራቸውን፣ የዐይናቸው ማረፊያና የልባቸው ደስታ የሆኑትን ወንድና ሴት ልጆቻቸውን ጭምር በምወስድባቸው ቀን፣

26 በዚያን ቀን፣ ያመለጠ ሰው ይህን ወሬ ሊነግርህ ወደ አንተ ይመጣል፤

27 በዚያን ቀን አፍህ ተከፍቶ ከእርሱ ጋር ትነጋገራለህ፤ ከዚያም በኋላ እንደ ድዳ አትሆንም፤ ምልክትም ትሆናቸዋለህ፤ እኔምእግዚአብሔርእንደሆንሁ ያውቃሉ።”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *