በአሞን ላይ የተነገረ ትንቢት
1 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ አሞናውያን አድርገህ፣ ትንቢት ተናገርባቸው፤
3 እንዲህም በላቸው፤ ‘የጌታ፣እግዚአብሔርንቃል ስሙ፤ ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “መቅደሴ በረከሰ ጊዜ፣ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ፣ የይሁዳም ቤት ተማርኮ በተወሰደ ጊዜ፣ ‘እሰይ’ ብላችኋልና፣
4 ለምሥራቅ ሕዝብ ትገዙ ዘንድ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ እነርሱም በመካከላችሁ ይሰፍራሉ፤ ድንኳኖቻቸውንም በዚያ ይተክላሉ፤ ፍሬያችሁን ይበላሉ፤ ወተታችሁንም ይጠጣሉ።
5 የራባን ከተማ የግመሎች መሰማሪያ፣ አሞንንም የበጎች መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ።”
6 ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላልና፤ “በልባችሁ ክፋት ሁሉ፣ በእስራኤል ውድቀት ላይ በመደሰት በእጃችሁ አጨብጭባችኋልና፤ በመዝለልም ጨፍራችኋልና
7 ክንዴን በእናንተ ላይ አነሣለሁ፤ በአሕዛብ እንድትበዘበዙ አደርጋለሁ፤ ከሕዝቦች መካከል አውጥቼ፣ ከአገሮችም ለይቼ አጠፋችኋለሁ፤ እደመስሳችኋለሁም። በዚያን ጊዜ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”
በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት
8 “ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘ሞዓብና ሴይር፣ “እነሆ የይሁዳ ቤት እንደ ሌሎቹ አሕዛብ ሁሉ ሆነ” ብለዋልና፤
9 በምድሪቱ ድንበር ላይ ካሉትና ክብሯ ከሆኑት ከተሞች ከቤት የሺሞት፣ ከበአልሜዎንና ከቂርያታይም ጀምሬ የሞዓብን ዐምባ እገልጣለሁ።
10 ሞዓባውያንንም ከአሞናውያን ጋር ይገዙላቸው ዘንድ ለምሥራቅ ሕዝብ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ አሞናውያን በአሕዛብ ዘንድ ከእንግዲህ መታሰቢያ አይኖራቸውም።
11 ሞዓብንም እቀጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”
በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት
12 “ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘ኤዶም የይሁዳን ቤት ተበቅሎአልና፤ በዚህም በደለኛ ሆኖአልና፤
13 ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ክንዴን በኤዶም ላይ አነሣለሁ፤ ሰዎቹንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ፤ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከቴማንም ጀምሮ እስከ ድዳን ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ።
14 በሕዝቤ በእስራኤል አማካይነት ኤዶምን እበቀላለሁ፤ እነርሱም እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴ መጠን በኤዶም ሕዝብ ላይ ያደርጋሉ፤ ኤዶማውያንም በቀሌን ያውቃሉ፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።’ ”
በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት
15 “ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘ፍልስጥኤማውያን በቂም ተነሣሥተው በክፉ ልብ ተበቅለዋልና፣ ይሁዳንም በቈየ ጠላትነት ለማጥፋት ፈልገዋልና፤
16 ስለዚህ ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ክንዴን በፍልስጥኤማውያን ላይ አነሣለሁ፤ ከሊታውያንንም እቈርጣለሁ፤ በባሕሩ ጠረፍ ላይ የቀሩትንም አጠፋለሁ።
17 በታላቅ በቀል እበቀላቸዋለሁ፤ በመዓቴም እቀጣቸዋለሁ፤” በምበቀላቸውም ጊዜ፣ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”