በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት
1 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ሴይር ተራራ አዙር፤ ትንቢትም ተናገርበት፤
3 እንዲህም በል፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ የሴይር ተራራ ሆይ፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ እጄን በአንተ ላይ እዘረጋለሁ፤ ባድማና ጠፍ አደርግሃለሁ።
4 ከተሞችህን ፍርስራሽ አደርጋቸዋለሁ፤ ባድማ ትሆናለህ፤ ከዚያም እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃለህ።
5 “ ‘እስራኤላውያን ቅጣታቸው እጅግ መራራ ከሆነ ደረጃ ላይ ደርሶ ፍዳቸውን በሚቀበሉበት ጊዜ፣ የጥንቱን ቂም ቋጥረህ ለሰይፍ ስለ ዳረግሃቸው፤
6 በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር፤ ለደም ማፍሰስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ እርሱም ያሳድድሃል። ደም ማፍሰስን ስላልጠላህ፣ ደም ማፍሰስ ያሳድድሃል።
7 የሴይርን ተራራ ባድማና ጠፍ አደርጋለሁ፤ በእርሱም ላይ የሚወጡትንና የሚወርዱትን አስቀራለሁ።
8 ተራሮችህን በሬሳ እሞላለሁ፤ በሰይፍ የተገደሉት ሁሉ በተራሮችህ፣ በሸለቆዎችህና በውሃ መውረጃዎችህ ሁሉ ላይ ይወድቃሉ።
9 ለዘላለም ባድማ አደርግሃለሁ፤ ከተሞችህ መኖሪያ አይሆኑም። ከዚያም እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
10 “ ‘እኔእግዚአብሔርበዚያ እያለሁ፣ “እነዚህ ሁለት ሕዝቦችና ሁለት አገሮች የእኛ ይሆናሉ፤ እኛም እንወርሳቸዋለን።” ብለሃልና፤
11 ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር፤ከጥላቻችሁ የተነሣ በእነርሱ ላይ በገለጣችሁት ቍጣና ቅናት ልክ እፈርድባችኋለሁ፤ በእናንተም ላይ በምፈርድበት ጊዜ፣ ማንነቴ በእነርሱ መካከል እንዲታወቅ አደርጋለሁ።
12 ከዚያም ስለ እስራኤል ተራሮች፣ “ጠፍ ሆነዋል፤ ቦጫጭቀን እንድንበላቸው ለእኛ ተሰጥተዋል” ብለህ በንቀት የተናገርኸውን እኔእግዚአብሔርእንደ ሰማሁ በዚያን ጊዜ ታውቃለህ።
13 በእኔ ላይ ታብየሃል፤ በድፍረትም በእኔ ላይ ተናግረሃል፤ እኔም ሰምቼዋለሁ።
14 ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ መላዪቷ ምድር በምትደሰትበት ጊዜ አንተን ባድማ አደርግሃለሁ።
15 የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ በሆነች ጊዜ ስለ ተደሰትህ፣ እኔም እንዲሁ አደርግብሃለሁ። የሴይር ተራራ ሆይ፤ አንተና መላዋ ኤዶም ባድማ ትሆናላችሁ፤ ከዚያም እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ያውቃሉ።