በክፉ ጊዜ የቀረበ ጸሎት
ባዘነና ልመናውን በእግዚአብሔር ፊት ባፈሰሰ ጊዜ፣ የተጨነቀ ሰው ጸሎት
1 እግዚአብሔርሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤
ጩኸቴም ወደ አንተ ይድረስ።
2 በመከራዬ ቀን፣ ፊትህን ከእኔ አትሰውር፤
ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤
በጠራሁህ ቀን ፈጥነህ መልስልኝ።
3 ዘመኔ እንደ ጢስ ተኖ አልቆአልና፤
ዐጥንቶቼም እንደ ማንደጃ ግለዋል።
4 ልቤ ዋግ እንደ መታው ሣር ደርቆአል፤
እህል መብላትም ዘንግቻለሁ።
5 ከጩኸቴ ድምፅ የተነሣ፣
ዐጥንቴ ከቈዳዬ ጋር ተጣበቀ።
6 የምድረ በዳ እርኩም መሰልሁ፤
በፍርስራሽ መካከል እንዳለ ጒጒት ሆንሁ።
7 ያለ እንቅልፍ አድራለሁ፤
በቤቴ ጒልላት ላይ እንዳለ ብቸኛ ወፍ ሆንሁ።
8 ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ ይዘልፉኛል፤
የሚያክፋፉኝም ስሜን እንደ ርግማን ቈጥረውታል።
9 ዐመድ እንደ እህል ቅሜአለሁና፤
መጠጤንም ከእንባ ጋር ቀላቅያለሁ።
10 ከቍጣህና ከመዓትህ የተነሣ፣
ወደ ላይ አንሥተኸኝ የነበርሁትን መልሰህ ጣልኸኝ።
11 ዘመኖቼ እንደ ምሽት ጥላ ናቸው፤
እኔም እንደ ሣር ደርቄአለሁ።
12 እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ ግን ለዘላለም በዙፋንህ ተቀምጠሃል፤
ስምህም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
13 ትነሣለህ፤ ጽዮንንም በርኅራኄ ዐይን ታያለህ፤
ለእርሷ በጎነትህን የምታሳይበት ዘመን ነውና፤
የተወሰነውም ጊዜ ደርሶአል።
14 አገልጋዮችህ በድንጋዮቿ ደስ ይሰኛሉ፤
ለዐፈሯም ይሳሳሉ።
15 ሕዝቦችየእግዚአብሔርንስም፣
የምድርም ነገሥታት ሁሉ ክብርህን ይፈራሉ።
16 እግዚአብሔርጽዮንን መልሶ ይሠራታልና፤
በክብሩም ይገለጣል።
17 እርሱ ወደ ችግረኞች ጸሎት ይመለከታል፤
ልመናቸውንም አይንቅም።
18 ወደ ፊት የሚፈጠር ሕዝብእግዚአብሔርንያወድስ ዘንድ፣
ይህ ለመጪው ትውልድ እንዲህ ተብሎ ይጻፍ፤
19 “እግዚአብሔርበከፍታ ላይ ካለው መቅደሱ ወደ ታች ተመልክቶአልና፤
ከሰማይም ሆኖ ምድርን አይቶአል፤
20 ይኸውም የእስረኞችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ፣
ሞት የተፈረደባቸውንም ያድን ዘንድ ነው።”
21 ስለዚህየእግዚአብሔርስም በጽዮን፣
ምስጋናውም በኢየሩሳሌም ይታወጃል፤
22 ይህም፣ ሕዝቦችና መንግሥታት፣
እግዚአብሔርንለማምለክ በአንድነት ሲሰበሰቡ ይሆናል።
23 ብርታቴን መንገድ ላይ ቀጨው፤
ዕድሜዬንም ባጭሩ አስቀረው።
24 እኔም እንዲህ አልሁ፤
“አምላኬ ሆይ፤ በዘመኔ እኵሌታ አትውሰደኝ፤
ዘመናትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራሉ።
25 አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤
ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው።
26 እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤
ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፤
እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፤
እነርሱም ወዲያ ይጣላሉ።
27 አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤
ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።
28 የአገልጋዮችህ ልጆች ተደላድለው ይኖራሉ፤
ዘራቸውም በፊትህ ጸንቶ ይኖራል።