ብሔራዊ ኑዛዜ
1 ሃሌ ሉያ
ቸር ነውና፣እግዚአብሔርንአመስግኑ፤
ምሕረቱም ለዘላለም ነውና።
2 ስለእግዚአብሔርታላቅ ሥራ ማን ሊናገር ይችላል?
ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ተናግሮ ይጨርሳል?
3 ፍትሕ እንዳይዛነፍ የሚጠብቁ፣
ጽድቅን ሁል ጊዜ የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው።
4 እግዚአብሔርሆይ፤ ለሕዝብህ ሞገስ ስታድል አስበኝ፤
በምታድናቸውም ጊዜ ርዳኝ፤
5 ይኸውም የምርጦችህን ብልጽግና አይ ዘንድ፣
በሕዝብህ ደስታ ደስ ይለኝ ዘንድ፣
ከርስትህም ክብር የተነሣ እጓደድ ዘንድ ነው።
6 እኛም እንደ አባቶቻችን ኀጢአት ሠራን፤
በደልን፤ ክፉም አደረግን።
7 አባቶቻችን በግብፅ ሳሉ፣
ታምራትህን አላስተዋሉም፤
የምሕረትህን ብዛት አላሰቡም፤
በባሕሩ አጠገብ፣ ገና ቀይ ባሕርአጠገብ ዐመፁብህ።
8 እርሱ ግን የኀይሉን ታላቅነት ለማሳወቅ፣
ስለ ስሙ አዳናቸው።
9 ቀይ ባሕርን ገሠጸ፤ እርሱም ደረቀ፤
በምድረ በዳ እንደሚታለፍ በጥልቅ ውሃ መካከል መራቸው።
10 ከባለጋራቸው እጅ አዳናቸው፤
ከጠላትም እጅ ታደጋቸው።
11 ባላንጦቻቸውን ውሃ ዋጣቸው፤
ከእነርሱም አንድ አልተረፈም።
12 ከዚህ በኋላ የተስፋ ቃሉን አመኑ፤
በዝማሬም አመሰገኑት።
13 ነገር ግን ያደረገውን ወዲያውኑ ረሱ፤
በምክሩም ለመሄድ አልታገሡም።
14 በምድረ በዳ እጅግ መመኘት አበዙ፤
በበረሓም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት።
15 እርሱም የለመኑትን ሰጣቸው፤
ዳሩ ግን የሚያኰሰምን ሕመም ሰደደባቸው።
16 በሰፈር በሙሴ ላይ፣
ለእግዚአብሔርበተቀደሰውም በአሮን ላይ ቀኑ።
17 ምድር ተከፍታ ዳታንን ዋጠች፤
የአቤሮንን ወገን ሰለቀጠች።
18 እሳት በጉባኤያቸው መካከል ነደደ፤
ነበልባሉም ክፉዎችን ፈጅቶ አስወገደ።
19 በኮሬብ ጥጃ ሠሩ፤
ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ።
20 ክብራቸው የሆነውንም ሣር በሚበላ፣
በበሬ ምስል ለወጡ።
21 በግብፅ ታላቅ ነገር ያደረገውን፣
ያዳናቸውን አምላክ ረሱ፤
22 እርሱ ግን በካም ምድር ድንቅ ሥራ፣
በቀይ ባሕርም አስደናቂ ነገር አደረገ።
23 ስለዚህ በመቅሠፍቱ እንዳያጠፋቸው ይመለስ ዘንድ፣
እርሱ የመረጠው ሙሴ በመካከል ገብቶ፣
በፊቱ ባይቆም ኖሮ፣
እንደሚያጠፋቸው ተናግሮ ነበር።
24 ከዚያም በኋላ መልካሚቱን ምድር ናቁ፤
የተስፋ ቃሉንም አላመኑም።
25 በድንኳኖቻቸው ውስጥ አጒረመረሙ፤
የእግዚአብሔርንምድምፅ አላዳመጡም።
26 በምድረ በዳ ሊጥላቸው፣
እጁን አንሥቶ ማለ፤
27 ዘራቸውንም በሕዝቦች መካከል ሊጥል፣
ወደ ተለያየ ምድርም እንደሚበትናቸው ማለ።
28 ራሳቸውን ከብዔል ፌጎር ጋር አቈራኙ፤
ለሙታን የተሠዋውን መሥዋዕት በሉ፤
29 በሥራቸውምእግዚአብሔርንአስቈጡት፤
ቸነፈርም በላያቸው መጣ።
30 ፊንሐስም ተነሥቶ ጣልቃ ገባ፤
ቸነፈሩም ተገታ፤
31 ይህም ከትውልድ እስከ ትውልድ፣
ለዘላለም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።
32 ደግሞም በመሪባ ውሃ አጠገብእግዚአብሔርንአስቈጡት፤
ሙሴም ከእነርሱ የተነሣ ተቸገረ፤
33 የእግዚአብሔርንምመንፈስ ስላስመረሩት፣
ሙሴ የማይገባ ቃል ከአንደበቱ አወጣ።
34 እግዚአብሔርባዘዛቸው መሠረት፣
ሕዝቦችን ከማጥፋት ወደ ኋላ አሉ፤
35 እንዲያውም ከሕዝቦቹ ጋር ተደባለቁ፤
ልማዳቸውንም ቀሠሙ፤
36 ጣዖቶቻቸውንም አመለኩ፤
ይህም ወጥመድ ሆነባቸው።
37 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን
ለአጋንንት ሠዉ።
38 የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ደም፣
ለከነዓን ጣዖታት የሠዉአቸውን፣
ንጹሕ ደም አፈሰሱ፤
ምድሪቱም በደም ተበከለች።
39 በተግባራቸው ረከሱ፤
በድርጊታቸውም አመንዝሮች ሆኑ።
40 ስለዚህየእግዚአብሔርቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤
ርስቱንም ተጸየፈ።
41 ለአሕዛብ አሳልፎ ሰጣቸው፤
ጠላቶቻቸውም በላያቸው ሠለጠኑ።
42 ጠላቶቻቸው ጨቈኗቸው፤
በሥልጣናቸውም ሥር አዋሏቸው።
43 እርሱ ብዙ ጊዜ ታደጋቸው፤
እነርሱ ግን ዐመፃን የሙጥኝ አሉ፤
በኀጢአታቸውም ተዋረዱ።
44 ሆኖም ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ፣
ጭንቀታቸውን ተመለከተ፤
45 ለእነርሱም ሲል ቃል ኪዳኑን አሰበ፤
እንደ ምሕረቱም ብዛት ከቍጣው ተመለሰ።
46 የማረኳቸው ሁሉ፣
እንዲራሩላቸው አደረገ።
47 አምላካችንእግዚአብሔርሆይ፤ አድነን፤
ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እናቀርብ ዘንድ፣
አንተን በመወደስ እንጓደድ ዘንድ፣
ከሕዝቦች መካከል ሰብስበህ አምጣን።
48 የእስራኤል አምላክእግዚአብሔር፣
ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤
ሕዝብም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
ሃሌ ሉያ።