መሲሑ ንጉሥና ካህን
የዳዊት መዝሙር
1 እግዚአብሔርጌታዬን፣
“ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ፣
እስከማደርግልህ ድረስ፣
በቀኜ ተቀመጥ” አለው።
2 እግዚአብሔርብርቱ በትርህን ከጽዮን ወደ ውጭ ይሰዳል፤
አንተም በጠላቶችህ መካከል ሆነህ ትገዛለህ።
3 ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣
ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል፤
ከንጋት ማሕፀን፣
በቅዱስ ግርማ ደምቀህ፣
የጐልማሳነትህን ልምላሜእንደ ጠል ትቀበላለህ።
4 “እንደ መልከጼዴቅ ሥርዐት፤
አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ብሎ፣
እግዚአብሔርምሎአል፤
እርሱ ሐሳቡን አይለውጥም።
5 ጌታ በቀኝህ ነው፤
በቍጣውም ቀን ነገሥታትን ያደቃቸዋል።
6 በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤
በየአገሩ ያሉትንም ራሶች ከስክሶ ሬሳ በሬሳ ያደርጋቸዋል።
7 መንገድዳር ካለች ፈሳሽ ውሃ ይጠጣል፤
ስለዚህ ራሱን ቀና ያደርጋል።