መዝሙር 140

በክፉዎች ላይ የቀረበ ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔርሆይ፤ ከክፉ ሰዎች አድነኝ፤

ከዐመፀኞችም ሰዎች ጠብቀኝ፤

2 እነርሱ በልባቸው ክፉ ነገር ያውጠነጥናሉ፤

በየዕለቱም ጦርነት ይጭራሉ።

3 ምላሳቸውን እንደ እባብ ያሾላሉ፤

ከከንፈራቸውም በታች የእፉኝት መርዝ አለ።ሴላ

4 እግዚአብሔርሆይ፤ ከክፉዎች እጅ ጠብቀኝ፤

እግሮቼንም ለመጥለፍ ከሚያደቡ ዐመፀኞች ሰውረኝ።

5 ትዕቢተኞች ወጥመድ በስውር አስቀመጡብኝ፤

የመረባቸውን ገመድ ዘረጉብኝ፤

በመንገዴም ላይ አሽክላ አኖሩ።ሴላ

6 እግዚአብሔርሆይ፤ “አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁ፤

እግዚአብሔርሆይ፤ የልመና ጩኸቴን ስማ።

7 ብርቱ አዳኝ የሆንህ፣ ጌታእግዚአብሔርሆይ፤

በጦርነት ዕለት የራስ ቍር ሆንኸኝ።

8 እግዚአብሔርሆይ፤ የክፉዎች ምኞት አይፈጸም፤

በትዕቢትም እንዳይኵራሩ፣

ዕቅዳቸው አይሳካ።ሴላ

9 ዙሪያዬን የከበቡኝ ሰዎች ራስ፣

የከንፈራቸው መዘዝ ይጠምጠምበት።

10 የእሳት ፍም በላያቸው ይውረድ፤

ዳግመኛም እንዳይነሡ ወደ እሳት ይጣሉ፤

ማጥ ወዳለበት ጒድጓድ ይውደቁ።

11 ምላሰኛ በምድሪቱ ጸንቶ አይኑር፤

ዐመፀኛውን ሰው ክፋት አሳዶ ያጥፋው።

12 እግዚአብሔርለድኻ ፍትሕን እንደሚያስከብር፣

ለችግረኛውም ትክክለኛ ፍርድን እንደሚሰጥ ዐውቃለሁ።

13 ጻድቃን በእውነት ስምህን ያመሰግናሉ፤

ቅኖችም በፊትህ ይኖራሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *