የክፉዎችን ድሎት ላለመመኘት የቀረበ ጸሎት
1 እግዚአብሔርሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤ ፈጥነህ ድረስልኝ፤
ወደ አንተ ስጣራም ድምፄን ስማ።
2 ጸሎቴ በፊትህ እንደ ዕጣን ትቈጠርልኝ፤
እጄን ማንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።
3 እግዚአብሔርሆይ፤ ለአፌ ጠባቂ አድርግ፤
የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ።
4 ከዐመፀኞች ጋር፣
በክፉ ሥራ እንዳልተባበር፣
ልቤን ወደ ክፉ አታዘንብል፤
ከድግሳቸውም አልቋደስ።
5 ጻድቅሰው ይቅጣኝ፤ ይህ በጎነት ነው፤
ይገሥጸኝም፤ በራሴ ላይ እንደሚፈስ ዘይት ነው፤
ራሴም ይህን እንቢ አይልም።
ጸሎቴ ግን በክፉዎች ተግባር ላይ ነው፤
6 ሹማምታቸው ከገደል አፋፍ ቍልቍል ይወረወራሉ፣
ቃሌ የምታረካ ናትና፣ ይሰሟታል።
7 ደግሞም፣ “ሰው ምድርን እንደሚያርስና ዐፈሩን እንደሚፈረካክስ፣
እንዲሁ ዐጥንታችን በሲኦልአፋፍ ላይ ተበታተነ” ይላሉ።
8 ጌታእግዚአብሔርሆይ፤ ዐይኖቼ ግን ወደ አንተ ይመለከታሉ፤
መጠጊያዬም አንተ ነህ፤ እንግዲህ ነፍሴን አትተዋት።
9 ከዘረጉብኝ ወጥመድ፣
ከክፉ አድራጊዎችም አሽክላ ጠብቀኝ።
10 እኔ ብቻ በደኅና ሳመልጥ፣
ክፉዎቹ በገዛ ወጥመዳቸው ይውደቁ።