የድል መዝሙር
1 ሃሌ ሉያ።
ለእግዚአብሔርአዲስ ቅኔ ተቀኙ፤
ምስጋናውንም በቅዱሳን ጉባኤ ዘምሩ።
2 እስራኤል በፈጣሪው ደስ ይበለው፤
የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤት ያድርጉ።
3 ስሙን በሽብሰባ ያመስግኑ፤ በከበሮና በመሰንቆ ይዘምሩለት።
4 እግዚአብሔርበሕዝቡ ደስ ይለዋልና፤
የዋሃንንም በማዳኑ ውበት ያጐናጽፋል።
5 ቅዱሳን በዚህ ክብር ይጓደዱ፤
በመኝታቸውም ላይ እልል እያሉ ይዘምሩ።
6 የአምላክ ውዳሴ በአንደበታቸው፣
ባለ ሁለት ልሳን ሰይፍም በእጃቸው ይሁን፤
7 በዚህ ሕዝቦችን ይበቀላሉ፤
ሰዎችንም ይቀጣሉ፤
8 ነገሥታታቸውን በሰንሰለት፣
መኳንንታቸውንም በእግር ብረት ያስራሉ፤
9 ይህም በእነርሱ ላይ የተጻፈውን ፍርድ ለመፈጸም ነው።
ለቅዱሳኑም ሁሉ ይህች ክብር ናት።
ሃሌ ሉያ።