ጸሎት ለንጉሡ
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር
1 እግዚአብሔርበጭንቅ ቀን ይስማህ፤
የያዕቆብም አምላክ ስም ይጠብቅህ።
2 ከመቅደሱ ረድኤት ይላክልህ፤
ከጽዮንም ደግፎ ይያዝህ።
3 ቍርባንህን ሁሉ ያስብልህ፤
የሚቃጠል መሥዋዕትህን ይቀበልልህ።ሴላ
4 የልብህን መሻት ይስጥህ፤
ዕቅድህን ሁሉ ያከናውንልህ።
5 በአንተ ድል ደስ ይበለን፤
በአምላካችን ስም አርማችንን ከፍ እናደርጋለን፤
እግዚአብሔርየለመንኸውን ሁሉ ይፈጽምልህ።
6 እግዚአብሔር፣የቀባውን እንደሚያድን
አሁን ዐወቅሁ፤
የማዳን ኀይል ባለው ቀኝ እጁ፣
ከተቀደሰው ሰማይ ይመልስለታል።
7 እነዚህ በሰረገላ፣ እነዚያ በፈረስ ይመካሉ፤
እኛ ግን ትምክህታችን የአምላካችንየእግዚአብሔርስም ነው።
8 እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፤
እኛ ግን ተነሣን፤ ጸንተንም ቆምን።
9 እግዚአብሔር ሆይ፤ ንጉሥን አድን፤
እኛም በጠራንህ ቀን ስማን።