መዝሙር 21

ምስጋና ስለ ንጉሡ

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔርሆይ፤ ንጉሥ በኀይልህ ደስ ይለዋል፤

በምትሰጠውም ድል እጅግ ሐሤት ያደርጋል።

2 የልቡን መሻት ሰጠኸው፤

የከንፈሮቹንም ልመና አልከለከልኸውም።ሴላ

3 መልካም በረከት ይዘህ በመንገዱ ላይ ጠብቀኸው፤

የንጹሕ ወርቅ ዘውድም በራሱ ላይ ደፋህለት።

4 ሕይወትን ለመነህ፤

ረዥም ዘመናትንም እስከ ዘላለም ሰጠኸው።

5 ባቀዳጀኸው ድል ክብሩ ታላቅ ሆነ፤

ክብርንና ሞገስን አጐናጸፍኸው።

6 ዘላለማዊ በረከትን ሰጠኸው፤

ከአንተ ዘንድ በሚገኝ ፍስሓም ደስ አሰኘኸው፤

7 ንጉሡበእግዚአብሔርተማምኖአልና፤

ከልዑልም ጽኑ ፍቅር የተነሣ፣

ከቆመበት አይናወጥም።

8 እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታገኛቸዋለች፤

ቀኝ እጅህም የሚጠሉህን ፈልጋ ትይዛለች።

9 በምትገለጥበት ጊዜ፣

እሳት እንደሚንቀለቀልበት ምድጃ ታደርጋቸዋለህ፤

እግዚአብሔርበመዓቱ እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል፤

እሳቱም ሙጥጥ አድርጋ ትበላቸዋለች።

10 ዘራቸውን ከምድር፣

ዘር ማንዘራቸውንም ከሰው ልጆች መካከል ታጠፋለህ።

11 ክፋት ቢያስቡብህ፣

ተንኰል ቢወጥኑብህም አይሳካላቸውም፤

12 በመጡበት ትመልሳቸዋለህና፤

ቀስትህንም በፊታቸው ላይ ታነጣጥራለህ።

13 እግዚአብሔርሆይ፤ በብርታትህ ከፍ ከፍ በል፤

ኀይልህን እናወድሳለን፤ እንዘምራለንም።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *