የንጹሕ ሰው ጸሎት
የዳዊት መዝሙር
1 እግዚአብሔርሆይ፤ ያለ ነቀፋ እንደ መሆኔ፣
አንተው ፍረድልኝ።
ወዲያ ወዲህ ሳልልም፣
በእግዚአብሔርታምኛለሁ።
2 እግዚአብሔርሆይ፤ ፈትነኝ፤
መርምረኝም፤
ልቤንና ውስጤን መርምር፤
3 ምሕረትህ ከፊቴ አልተለየምና፣
በእውነትህም ተመላለስሁ።
4 ከማይረቡ ጋር አልተቀመጥሁም፤
ከግብዞችም ጋር አልተባበርሁም።
5 የክፉዎችን ማኅበር ተጸየፍሁ፤
ከዐመፀኞችም ጋር አልቀመጥም።
6 እጆቼን በየዋህነት እታጠባለሁ፤
እግዚአብሔርሆይ፤ መሠዊያህንም እዞራለሁ፤
7 የምስጋናን ድምፅ አሰማ ዘንድ፣
ታምራትህንም አወራ ዘንድ ነው።
8 እግዚአብሔርሆይ፤ የምትኖርበትን ቤት፣
የክብርህን ማደሪያ ቦታ ወደድሁ።
9 ነፍሴን ከኀጢአተኞች ጋር፣
ሕይወቴንም ከደም አፍሳሾች ጋር አታስወግዳት።
10 በእነርሱ እጅ የተንኰል ዕቅድ አለ፤
ቀኝ እጃቸውም ጒቦን ያጋብሳል።
11 እኔ ግን በተአማኒ ሕይወት እጓዛለሁ፤
አድነኝ፤ ምሕረትንም አድርግልኝ።
12 እግሮቼ በደልዳላ ስፍራ ቆመዋል፤
በታላቅ ጉባኤ መካከልምእግዚአብሔርንእባርከዋለሁ።