ልመናና ምስጋና
የዳዊት መዝሙር
1 እግዚአብሔርሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤
ዐለቴ ሆይ፤ ሰምተህ እንዳልሰማ አትሁንብኝ፤
አንተ ዝም ካልኸኝ፤
ወደ ጒድጓድ እንደሚወርዱ እሆናለሁ።
2 ለርዳታ በጮኽሁ ጊዜ፣
ወደ ቅዱስ ማደሪያህ፣
እጆቼን በዘረጋሁ ጊዜ፣
የልመናዬን ቃል ስማ።
3 በልባቸው ተንኰል እያለ፣
ከባልንጀሮቻቸው ጋር በሰላም ከሚናገሩ፣
ከክፉ አድራጊዎችና፣
ከዐመፃ ሰዎች ጋር ጐትተህ አትውሰደኝ።
4 እንደ ሥራቸው፣
እንደ ክፉ ተግባራቸው ክፈላቸው፤
እንደ እጃቸው ሥራ ስጣቸው፤
አጸፋውን መልስላቸው።
5 ለእግዚአብሔርሥራ ግድ ስለሌላቸው፣
ለእጆቹም ተግባራት ስፍራ ስላልሰጡ፣
እርሱ ያፈርሳቸዋል፤
መልሶም አይገነባቸውም።
6 የልመናዬን ቃል ሰምቶአልና፣
እግዚአብሔርየተባረከ ይሁን።
7 እግዚአብሔርብርታቴና ጋሻዬ ነው፤
ልቤ በእርሱ ይታመናል፤ እርሱም ዐግዞኛል፤
ልቤ ሐሤት አደረገ፤
በዝማሬም አመሰግነዋለሁ።
8 እግዚአብሔርለሕዝቡ ብርታታቸው ነው፤
ለቀባውም የመዳን ዐምባ ነው።
9 ሕዝብህን አድን፤ ርስትህንም ባርክ፤
እረኛ ሁናቸው፤ ለዘላለሙም ዐቅፈህ ያዛቸው።