ከክፉ አደጋ የዳነ ሰው ምስጋና
ለቤተ መቅደሱ ምረቃ የተዘመረ፤ የዳዊት መዝሙር
1 እግዚአብሔርሆይ፤ ከታች አንሥተኸኛልና፣
ጠላቶቼም በላዬ እንዳይደሰቱ አድርገሃልና፣
ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።
2 እግዚአብሔርአምላኬ ሆይ፤ ትረዳኝ ዘንድ ወደ አንተ ጮኽሁ፤
አንተም ፈወስኸኝ።
3 እግዚአብሔርሆይ ነፍሴን ከሲኦልአወጣሃት፤
ወደ ጒድጓድ ከመውረድም መልሰህ ሕያው አደረግኸኝ።
4 እናንተ ቅዱሳኑ፤ለእግዚአብሔርዘምሩ፤
ቅዱስ ስሙንም አወድሱ።
5 ቊጣው ለዐጭር ጊዜ ነው፤
ቸርነቱ ግን እስከ ዕድሜ ልክ ነውና፤
ሌሊቱን በልቅሶ ቢታደርም፣
በማለዳ ደስታ ይመጣል።
6 እኔም በተረጋጋሁ ጊዜ፣
“ከቶ አልናወጥም” አልሁ።
7 እግዚአብሔርሆይ፤ በአንተ ሞገስ፣
ተራሮቼጸኑ፣
ፊትህን በሰወርህ ጊዜ ግን፣
ውስጤ ታወከ።
8 እግዚአብሔርሆይ፤ ወደ አንተ ተጣራሁ፤
ወደ ጌታም እንዲህ ብዬ ጮኽሁ፤
9 “በእኔ ወደ ጒድጓድ መውረድ፣
በመሞቴ ምን ጥቅም ይገኛል?
ዐፈር ያመሰግንሃልን?
ታማኝነትህንስ ይናገራልን?
10 እግዚአብሔርሆይ፤ ስማ፤ ማረኝም፤
እግዚአብሔርሆይ፤ ረዳት ሁነኝ።”
11 ዋይታዬን ወደ ሽብሸባ ለወጥህልኝ፤
ማቄን አውልቀህ ፍስሓን አለበስኸኝ፤
12 እንግዲህ ነፍሴ ታመስግንህ፤ ዝምም አትበል፤
እግዚአብሔርአምላኬ ሆይ፤ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ።