የመከራ ጊዜ ጸሎት
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር
1 እግዚአብሔርሆይ፤ በአንተ ተተግኛለሁ፤
እንግዲህ ዕፍረት ከቶ አይድረስብኝ፤
በጽድቅህም ታደገኝ።
2 ጆሮህን ወደ እኔ መልሰህ ስማኝ፤
ፈጥነህ አድነኝ፤
መጠጊያ ዐለት ሁነኝ፤
ታድነኝም ዘንድ ምሽግ ሁነኝ።
3 አንተ ዐለቴና መጠጊያዬ ነህና፣
ስለ ስምህ ስትል ምራኝ፤
መንገዱንም ጠቍመኝ።
4 አንተ መጠጊያዬ ነህና፣
በስውር ከተዘረጋብኝ ወጥመድ አውጣኝ።
5 መንፈሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ፤
እግዚአብሔርየእውነት አምላክ ሆይ፤
አንተ ተቤዠኝ።
6 ለከንቱ ጣዖታት ስፍራ የሚሰጡትን ጠላሁ፤
ነገር ግንበእግዚአብሔርታመንሁ።
7 በምሕረትህ ደስ እሰኛለሁ፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤
መከራዬን አይተሃልና፤
የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል።
8 ለጠላት አሳልፈህ አልሰጠኸኝም፤
ነገር ግን እግሮቼን ሰፊ ቦታ ላይ አቆምሃቸው።
9 እግዚአብሔርሆይ፤ በመከራ ውስጥ ነኝና ማረኝ፤
ዐይኖቼ በሐዘን ደክመዋል፤
ነፍስና ሥጋዬም ዝለዋል።
10 ሕይወቴ በመጨነቅ፣
ዕድሜዬም በመቃተት ዐለቀ፤
ከመከራዬየተነሣ ጒልበት ከዳኝ፤
ዐጥንቴም በውስጤ ሟሟ።
11 ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ፣
ለጎረቤቶቼ መዘባበቻ፣
ለወዳጆቼ መሣለቂያ ሆኛለሁ፤
መንገድ ላይ የሚያገኙኝም ይሸሹኛል።
12 እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ፤
እንደ ተሰበረ የሸክላ ዕቃም ተቈጠርሁ።
13 የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁና፤
ዙሪያው ሁሉ ሽብር አለ፤
በእኔ ላይ ባሤሩ ጊዜ፣
ሕይወቴን ለማጥፋት ዶለቱ።
14 እግዚአብሔርሆይ፤ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ፤
“አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁም።
15 ዘመኔ ያለው በእጅህ ነው፤
ከጠላቶቼ እጅ ታደገኝ፤
ከሚያሳድዱኝም አድነኝ።
16 ፊትህን በአገልጋይህ ላይ አብራ፤
በምሕረትህም አድነኝ።
17 እግዚአብሔርሆይ፤
ወደ አንተ እጮኻለሁና አልፈር፤
ክፉዎች ግን ይፈሩ፤
ሲኦልገብተውም ጸጥ ይበሉ።
18 በጻድቁ ላይ በእብሪት የሚናገሩ፣
ትዕቢትንና ንቀትን የተሞሉ፣
ዋሾ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ።
19 በሰዎች ልጆች ፊት፣
ለሚፈሩህ ያስቀመጥሃት፣
መጠጊያ ላደረጉህም ያዘጋጀሃት፣
በጎነትህ ምንኛ በዛች!
20 ከሰዎች ሤራ፣
በማደሪያህ ውስጥ ትሸሽጋቸዋለህ፤
ከአንደበት ጭቅጭቅም፣
በድንኳንህ ውስጥ ትከልላቸዋለህ።
21 በተከበበች ከተማ ውስጥ፣
የሚያስደንቅ ምሕረቱን ያሳየኝ፣
እግዚአብሔርይባረክ።
22 እኔ በደነገጥሁ ጊዜ፣
“ከዐይንህ ፊት ተወግጃለሁ” አልሁ፤
አንተ ግን ወደ አንተ ስጮኽ፣
የልመናዬን ቃል ሰማህ።
23 እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣እግዚአብሔርንውደዱት!
እግዚአብሔርታማኞችን ይጠብቃል፤
ትዕቢተኞችን ግን ፈጽሞ ይበቀላቸዋል።
24 እግዚአብሔርንተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤
በርቱ፤ ልባችሁም ይጽና።