ግልጥ ኑዛዜ
የዳዊት ትምህርት
1 መተላለፉ ይቅር የተባለለት፣
ኀጢአቱም የተሸፈነለት፣
እንዴት ቡሩክ ነው!
2 እግዚአብሔርኀጢአቱን የማይቈጥርበት፣
በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው፣
እርሱ ቡሩክ ነው።
3 ቀኑን ሙሉ ከመቃተቴ የተነሣ፣
ዝም ባልሁ ጊዜ፣
ዐጥንቶቼ ተበላሹ፤
4 በቀንና በሌሊት፣
እጅህ ከብዳብኛለችና፤
ኀይሌም የበጋ ትኵሳት እንደላሰው ነገር፣
ከውስጤ ተሟጠጠ።ሴላ
5 ኀጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፤
በደሌንም አልሸሸግሁም፤
ደግሞም “መተላለፌንለእግዚአብሔርእናዘዛለሁ” አልሁ፤
አንተም የኀጢአቴን በደል፣
ይቅር አልህ።ሴላ
6 ስለዚህ ጻድቅ ሁሉ፣
በጭንቅ ጊዜ ወደ አንተ ይጸልይ፤
ኀይለኛ ጐርፍ አካባቢውን ቢያጥለቀልቅም፣
እርሱ አጠገብ አይደርስም።
7 አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤
ከመከራ ትጠብቀኛለህ፤
በድል ዝማሬም ትከበኛለህ።ሴላ
8 አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤
እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።
9 በልባብና በልጓም ካልተገሩ በቀር፣
ወደ አንተ እንደማይቀርቡት፣
ማስተዋል እንደሌላቸው፣
እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ።
10 የክፉዎች ዋይታ ብዙ ነው፤
በእግዚአብሔርየሚታመን ግን፣
ምሕረት ይከበዋል።
11 ጻድቃን ሆይ፤በእግዚአብሔርደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትም አድርጉ፤
ቅን ልብ ያላችሁም ሁሉ እልል በሉ።