የጻድቁና የክፉው ዕጣ ፈንታ
የዳዊት መዝሙር
1 ዐመፀኞችን በማየት አትሸበር፤
በክፉ አድራጊዎችም አትቅና፤
2 እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፤
እንደ ለምለም ቅጠልም ይጠወልጋሉ።
3 በእግዚአብሔርታመን፤ መልካምንም አድርግ፤
በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ።
4 በእግዚአብሔርደስ ይበልህ፤
የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።
5 መንገድህንለእግዚአብሔርዐደራ ስጥ፤
በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል፤
6 ጽድቅህን እንደ ብርሃን፣
ያንተን ፍትሕ እንደ ቀትር ፀሓይ ያበራዋል።
7 በእግዚአብሔርፊት ጸጥ በል፤
በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤
መንገዱ በተቃናለት፣
ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር።
8 ከንዴት ተቈጠብ፤ ቍጣንም ተወው፤
ወደ እኵይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ።
9 ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤
እግዚአብሔርንተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ።
10 ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤
ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም።
11 ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤
በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።
12 ክፉዎች በጻድቃን ላይ ያሤራሉ፤
ጥርሳቸውንም ያፋጩባቸዋል።
13 እግዚአብሔር ግን ይሥቅባቸዋል፤
ቀናቸው እንደ ደረሰ ያውቃልና።
14 ድኾችንና ችግረኞችን ለመጣል፣
አካሄዳቸው ቀና የሆነውንም ለመግደል፣
ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፤
ቀስታቸውንም ገተሩ።
15 ሰይፋቸው የገዛ ልባቸውን ይወጋል፤
ቀስታቸውም ይሰበራል።
16 የጻድቅ ጥቂት ሀብት፣
ከክፉዎች ብዙ ጥሪት ይበልጣል።
17 የክፉዎች ክንድ ይሰበራልና፤
ጻድቃንን ግን እግዚአብሔር ደግፎ ይይዛቸዋል።
18 እግዚአብሔርየንጹሐንን የሕይወት ዘመን ያውቃል፤
ርስታቸውም ለዘላለም ይኖራል።
19 በክፉ ጊዜ ዐንገት አይደፉም፤
በራብ ዘመንም ይጠግባሉ።
20 ክፉዎች ግን ይጠፋሉ፤
የእግዚአብሔርጠላቶች እንደ መስክ ውበት ይሆናሉ፤
ይጠፋሉ፤ እንደ ጢስም ተነው ይጠፋሉ።
21 ኀጢአተኛ ይበደራል፤ መልሶም አይከፍልም፤
ጻድቅ ግን ይቸራል።
22 እግዚአብሔርየባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤
እርሱ የሚረግማቸው ግን ይጠፋሉ።
23 የሰው አካሄድበእግዚአብሔርይጸናል፤
በመንገዱ ደስ ይለዋል።
24 ቢሰናከልም አይወድቅም፤
እግዚአብሔርበእጁ ደግፎ ይይዘዋልና።
25 ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤
ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣
ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም።
26 ሁል ጊዜ ቸር ነው፤ ያበድራልም፤
ልጆቹም የተባረኩ ይሆናሉ።
27 ከክፉ ራቅ፤ መልካሙንም አድርግ፤
ለዘላለምም ትኖራለህ።
28 እግዚአብሔርፍትሕን ይወዳልና፤
ታማኞቹንም አይጥልም፤
ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፤
የኀጢአተኛው ዘር ግን ይጠፋል።
29 ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤
በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።
30 የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤
አንደበቱም ፍትሐዊ ነገር ያወራል።
31 የአምላኩ ሕግ በልቡ አለ፤
አካሄዱም አይወላገድም።
32 ክፉዎች ጻድቁን ይከታተሉታል፤
ሊገድሉትም ይሻሉ።
33 እግዚአብሔርግን በእጃቸው አይጥለውም፤
ፍርድ ፊት ሲቀርብም አሳልፎ አይሰጠውም።
34 እግዚአብሔርንደጅ ጥና፤
መንገዱንም ጠብቅ፤
ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤
ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ።
35 ክፉና ጨካኙን ሰው፣
እንደ ሊባኖስ ዝግባ ለምልሞ አየሁት፤
36 ዳግመኛ በዚያ ሳልፍ፣ እነሆ፣ በቦታው አልነበረም፤
ብፈልገውም አልተገኘም።
37 ንጹሐንን ልብ በል፤ ቅኑንም አስተውል፤
የሰላም ሰው ተስፋ አለውና።
38 ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይጠፋሉ፤
የክፉዎችም ዘርይወገዳል።
39 የጻድቃን ድነትከእግዚአብሔርዘንድ ነው፤
በመከራ ጊዜም መጠጊያቸው እርሱ ነው።
40 እግዚአብሔርይረዳቸዋል፤
ይታደጋቸዋልም፤
ከክፉዎች እጅ ነጥቆ ያወጣቸዋል፤
እርሱን መጠጊያ አድርገዋልና ያድናቸዋል።