የሕመምተኛና የብቸኛ ሰው ጸሎት
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር
1 ለድኾች የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው፤
እርሱንምእግዚአብሔርበክፉ ቀን ይታደገዋል።
2 እግዚአብሔርይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል፤
በምድርም ላይ ይባርከዋል፤
ለጠላቶቹም ምኞትም አሳልፎ አይሰጠውም።
3 ታሞ ባለበት ዐልጋ ላይእግዚአብሔርይንከባከበዋል፤
በበሽታውም ጊዜ መኝታውን ያነጥፍለታል።
4 እኔም፣ “እግዚአብሔርሆይ፤ ምሕረት አድርግልኝ፤
አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት” አልሁ።
5 ጠላቶቼ በክፋት በመናገር፣ “የሚሞተው መቼ ነው? ስሙስ
የሚደመሰሰው ምን ቀን ነው?” ይላሉ።
6 ሊጠይቀኝ የሚመጣ ቢኖር፣
በልቡ ስድብ እያጠራቀመ፣ ከዐንገት በላይ ይናገራል፤
ወጥቶም ወሬ ይነዛል።
7 ጠላቶቼ ሁሉ ግንባር ፈጥረው ይንሾካሾኩብኛል፤
እንዲህ እያሉም፣
የከፋ ነገር በላዬ ያውጠነጥናሉ፤
8 “ክፉ ደዌ ይዞታል፤
ከእንግዲህም ከተኛበት አይነሣም።”
9 እንጀራዬን ተካፍሎኝ የበላ፣
የምተማመንበትም የቅርብ ወዳጄ፣
በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ።
10 እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ ግን ምሕረት አድርግልኝ፤
የእጃቸውን እንድከፍላቸው አስነሣኝ።
11 ጠላቴ በላዬ ድል አላገኘምና፣
እንደ ወደድኸኝ በዚህ አወቅሁ።
12 ስለ ጭንቀቴ ደግፈህ ይዘኸኛል፤
በፊትህም ለዘላለም ታኖረኛለህ።
13 የእስራኤል አምላክእግዚአብሔር፣
ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን፤
አሜን፤ አሜን።