በስደት ላይ ያለ ሌዋዊ ልቅሶ
1 አምላክ ሆይ፤ ፍረድልኝ፤
ከጽድቅ ከራቀ ሕዝብ ጋር ተሟገትልኝ፤
ከአታላዮችና ከክፉዎች ሰዎችም አድነኝ።
2 አምላክ ሆይ፤ አንተ ብርታቴ ነህና፣
ለምን ተውኸኝ?
ጠላትስ እያስጨነቀኝ፣
ለምን በሐዘን እመላለሳለሁ?
3 ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤
እነርሱ ይምሩኝ፤
ወደ ተቀደሰው ተራራህ፣
ወደ ማደሪያህ ያድርሱኝ።
4 እኔም ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ አቀናለሁ፤
ፍጹም ደስታዬ ወደ ሆነው አምላክ እሄዳለሁ፤
እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፣
በበገና አመሰግንሃለሁ።
5 ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ?
ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ?
ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፤
አዳኜና አምላኬን፣
ገና አመሰግነዋለሁና።