ለፍትሕ አምላክ የቀረበ አቤቱታ
ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ዜፋውያን ወደ ሳኦል መጥተው፣ “ዳዊት በእኛ ዘንድ ተደብቆአል” ባሉት ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ በስምህ አድነኝ፤
በኀይልህም ፍረድልኝ።
2 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማልኝ፤
የአፌንም ቃል አድምጥ።
3 ባዕዳን ተነሥተውብኛልና፤
ግፈኞች ነፍሴን ሽተዋታል፤
እግዚአብሔርንም ከምንም አልቈጠሩም።ሴላ
4 እነሆ፤ እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፤
ጌታም ደግፎ ይይዘኛል።
5 የገዛ ክፋታቸው በሚያደቡብኝ ላይ ይመለስባቸው፤
በቃልህ ታማኝ ነህና አጥፋቸው።
6 በበጎ ፈቃድ መሥዋዕት እሠዋልሃለሁ፤
እግዚአብሔርሆይ፤ መልካም ነውና፣
ለስምህ ምስጋና አቀርባለሁ፤
7 ከመከራ ሁሉ ታድጎኛልና፤
ዐይኔም የጠላቶቼን ውድቀት ለማየት በቅቶአል።