በጨካኝ ጠላቶች ዘንድ
ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዘመር፤ ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በዋሻ በነበረበት ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ።
1 ማረኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ማረኝ፤
ነፍሴ አንተን መጠጊያ አድርጋለችና፤
በክንፎችህ ሥር እጠለላለሁ።
2 ለእኔ ያሰበውን ወደሚፈጽምልኝ አምላክ፣
ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ።
3 ከሰማይ ልኮ ያድነኛል፤
የረገጡኝን ያዋርዳቸዋል፤ሴላ
እግዚአብሔር ምሕረቱንና ታማኝነቱን ይልካል።
4 ነፍሴ በአንበሶች ተከብባለች፤
በሚዘነጣጥሉ አራዊት መካከል ወድቄአለሁ፤
እነዚህም፣ ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፣
ምላሳቸውም የተሳለ ሰይፍ የሆኑ ሰዎች ናቸው።
5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤
ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትስፈን።
6 ለእግሬ ወጥመድን ዘረጉ፤
ነፍሴንም አጐበጧት፤
በመተላለፊያዬ ላይ ጒድጓድ ቈፈሩ፤
ነገር ግን ራሳቸው ገቡበት።ሴላ
7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው፤
ልቤ ጽኑ ነው፤
እቀኛለሁ፤ አዜማለሁ።
8 ነፍሴ ሆይ፤ ንቂ!
በገናና መሰንቆም ተነሡ
እኔም በማለዳ እነሣለሁ።
9 ጌታ ሆይ፤ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤
በሰዎችም መካከል እዘምርልሃለሁ፤
10 ምሕረትህ እስከ ሰማያት ከፍ ብላለችና፤
ታማኝነትህም እስከ ደመናት ትደርሳለች።
11 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤
ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትስፈን።