መዝሙር 59

ክፉዎችን በመቃወም የቀረበ ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዜም፤ ዳዊትን ለመግደል ሰዎች ቤቱን ከብበው እንዲጠብቁት ሳኦል በላካቸው ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ

1 አምላክ ሆይ፤ ከጠላቶቼ እጅ አድነኝ፤

ሊያጠቁኝ ከሚነሡብኝም ጠብቀኝ።

2 ከክፉ አድራጊዎች ታደገኝ፤

ደም ከተጠሙ ሰዎችም አድነኝ።

3 እነሆ በነፍሴ ላይ አድብተዋልና፤

እግዚአብሔርሆይ፤ ጨካኞች ያለ በደሌ፣ ያለ ኀጢአቴ

በላዬ ተሰብስበው ዶለቱብኝ።

4 እነርሱ ያለ በደሌ ሊያጠቁኝ ተዘጋጅተው መጡ፤

አንተ ግን ትረዳኝ ዘንድ ተነሥ፤ ሁኔታዬንም ተመልከት።

5 የሰራዊት አምላክ የሆንህ፣ አንተ የእስራኤል አምላክእግዚአብሔርሆይ፤

ሕዝቦችን ሁሉ ለመቅጣት ተነሥ፤

በተንኰላቸው በደል የሚፈጽሙትንም ሁሉ አትማራቸው።ሴላ

6 እንደ ውሻ እያላዘኑ፣

በምሽት ተመልሰው ይመጣሉ፤

በከተማዪቱም ዙሪያ ይራወጣሉ።

7 ከአፋቸው የሚወጣውን ተመልከት፤

ሰይፍ በከንፈራቸው ላይ አለ፤

“ማን ሊሰማን ይችላል?” ይላሉና።

8 እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ ግን ትሥቅባቸዋለህ፤

ሕዝቦችን ሁሉ በንቀት ታያቸዋለህ።

9 ብርታቴ ሆይ፤ አንተን እጠብቃለሁ፤

አምላክ ሆይ፤ አንተ መጠጊያዬ ነህና።

10 እግዚአብሔር በምሕረቱ ይገናኘኛል፤

አምላኬ የጠላቶቼን ውድቀት ያሳየኛል።

11 ጋሻችንጌታ ሆይ፤ አትግደላቸው፤

አለበለዚያ ሕዝቤ ይረሳል፤

በኀይልህ አንከራታቸው፤

ዝቅ ዝቅም አድርጋቸው።

12 ከአፋቸው ስለሚወጣው ኀጢአት፣

ከከንፈራቸውም ስለሚሰነዘረው ቃል፣

በትዕቢታቸው ይያዙ።

ስለ ተናገሩት መርገምና ውሸት፣

13 በቊጣ አጥፋቸው፤

ፈጽመህም አስወግዳቸው፤

በዚህም እግዚአብሔር የያዕቆብ ገዥ መሆኑ፣

እስከ ምድር ዳርቻ ይታወቃል።ሴላ

14 እንደ ውሻ እያላዘኑ፣

በምሽት ተመልሰው ይመጣሉ፤

በከተማዪቱም ዙሪያ ይራወጣሉ።

15 ምግብ ፍለጋ ይራወጣሉ።

ካልጠገቡም ያላዝናሉ።

16 እኔ ግን ስለ ኀይልህ እዘምራለሁ፤

በማለዳም ስለ ምሕረትህ እዘምራለሁ፤

አንተ መጠጊያዬ፣

በመከራም ቀን ዐምባዬ ነህና።

17 ብርታቴ ሆይ፤ ውዳሴ አቀርብልሃለሁ፤

እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መጠጊያዬ፣

የምትወደኝም አምላኬ ነህና።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *