የግዞተኛ ጸሎት
ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች የሚዘመር፤ የዳዊት መዝሙር
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴን ስማ፤
ጸሎቴንም አድምጥ።
2 ልቤ በዛለ ጊዜ፣
ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ እጣራለሁ፤
ከእኔ ይልቅ ከፍ ወዳለው ዐለት ምራኝ።
3 አንተ መጠጊያዬ፣
ከጠላትም የምተገንብህ ጽኑ ግንብ ሆነኸኛልና።
4 በድንኳንህ ለዘላለም ልኑር፤
በክንፎችህም ጥላ ልከለል።ሴላ
5 አምላክ ሆይ፤ ስእለቴን ሰምተሃልና፤
ስምህን የሚፈሩትንም ሰዎች ርስት ለእኔ ሰጠህ።
6 የንጉሡን ዕድሜ አርዝምለት፤
ዘመኑንም እስከ ብዙ ትውልድ ጨምርለት፤
7 በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይንገሥ፤
ይጠብቁት ዘንድ ምሕረትህንና ታማኝነትህን አዘጋጅለት።
8 ስለዚህ ለስምህ ዘወትር ውዳሴ አቀርባለሁ፤
ስእለቴንም በየጊዜው እፈጽማለሁ።