እግዚአብሔርን መፈለግ
በይሁዳ ምድረ በዳ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤
አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣
በደረቅና በተራቈተ ምድር፣
ነፍሴ አንተን ተጠማች፤
ሥጋዬም አንተን ናፈቀች።
2 ስለዚህ በመቅደስ ውስጥ አየሁህ፤
ኀይልህንና ክብርህንም ተመለከትሁ።
3 ምሕረትህ ከሕይወት ይበልጣልና፤
ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል።
4 እንግዲህ፣ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፤
በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ።
5 ነፍሴ በቅቤና በሥብ እንደሚረካ ሰው ትረካለች፤
አፌም በሚያዜሙ ከንፈሮች በደስታ ያወድስሃል።
6 በመኝታዬ አስብሃለሁ፤
ሌሊቱንም ሁሉ ስለ አንተ አሰላስላለሁ።
7 አንተ ረዳቴ ነህና፣
በክንፎችህ ሥር ተጠልዬ በደስታ እዘምራለሁ።
8 ነፍሴ አንተን የሙጥኝ ብላለች፤
ቀኝ እጅህም ደግፋ ይዛኛለች።
9 ነፍሴን ለማጥፋት የሚሹ ግን፣
ወደ ምድር ጥልቅ ይወርዳሉ፤
10 ለሰይፍ አልፈው ይሰጣሉ፤
የቀበሮዎችም ምግብ ይሆናሉ።
11 ንጉሥ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤
በእግዚአብሔርም ስም ቃል የሚገቡ ሁሉ ይከብራሉ፤
የሐሰተኞች አንደበትም ትዘጋለች።