የተሳዳቢዎች ቅጣት
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር
1 አምላክ ሆይ፤ የብሶት ቃሌን ስማ፤
ሕይወቴንም ከሚያስፈራ የጠላት ዛቻ ከልላት።
2 ከክፉዎች አድማ ሰውረኝ፤
ከዐመፀኞችም ሸንጎ ጋርደኝ።
3 እነርሱ ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ ይስላሉ፤
መርዘኛ ቃላቸውንም እንደ ፍላጻ ያነጣጥራሉ።
4 አሸምቀው ንጹሑን ሰው ይነድፉታል፤
ድንገት ይነድፉታል፤ አይፈሩምም።
5 ክፉ ተግባር ለማከናወን እርስ በርስ ይመካከራሉ፤
በስውር ወጥመድ ለመዘርጋት ይነጋገራሉ፤
“ማንስ ሊያየን ይችላል?”ይባባላሉ።
6 ግፍን ያውጠነጥናሉ፤
ደግሞም፣ “የረቀቀች ሤራ አዘጋጅተናል” ይላሉ፤
አቤት! ልቡ፣ አእምሮውም እንዴት ጥልቅ ነው!
7 እግዚአብሔር ግን በፍላጻው ይነድፋቸዋል፤
እነርሱም ድንገት ይቈስላሉ።
8 በገዛ ምላሳቸው ያሰናክላቸዋል፤
ጥፋትንም ያመጣባቸዋል፤
የሚያዩአቸውም ሁሉ በትዝብት ራሳቸውን ይነቀንቃሉ።
9 የሰው ልጆች ሁሉ ይፈራሉ፤
የእግዚአብሔርን ሥራ በይፋ ያወራሉ፤
ያደረገውንም በጥሞና ያሰላስላሉ።
10 ጻድቅበእግዚአብሔርደስ ይበለው፤
እርሱንም መጠጊያ ያድርገው፤
ልበ ቅኖችም ሁሉ ደስ ይበላቸው።