የመከር ጊዜ መዝሙር
ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች የሚዘመር፤ የዳዊት መዝሙር፤ ማኅሌት
1 እግዚአብሔር ይማረን፤ ይባርከን፤
ፊቱንም በላያችን ያብራ፤ሴላ
2 መንገድህ በምድር ላይ፣
ማዳንህም በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይታወቅ ዘንድ።
3 እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰዎች ያመስግኑህ፤
ሰዎች ሁሉ ምስጋና ያቅርቡልህ።
4 ለሕዝቦች በቅን ስለምትፈርድላቸው፣
ሰዎችንም በምድር ላይ ስለምትመራ፣
ሕዝቦች ደስ ይበላቸው፤ በእልልታም ይዘምሩ።ሴላ
5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰዎች ያመስግኑህ፤
ሰዎች ሁሉ ምስጋና ያቅርቡልህ።
6 ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤
እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።
7 እግዚአብሔር ይባርከናል፤
የምድርም ዳርቻዎች ሁሉ እርሱን ይፈሩታል።