መዝሙር 86

የመከራ ጊዜ ጸሎት

የዳዊት ጸሎት

1 እግዚአብሔርሆይ፤ ጆሮህን ወደ እኔ ጣል፤ ስማኝም፤

እኔ ድኻና ችግረኛ ነኝና።

2 ለአንተ የተለየሁ ሰው ነኝና ነፍሴን ጠብቃት፤

አንተ አምላኬ ሆይ፤

በአንተ የታመነብህን ባሪያህን አድን።

3 ጌታ ሆይ፤ ማረኝ፤

ቀኑን ሙሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና።

4 የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፤

ጌታ ሆይ፤ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና።

5 ጌታ ሆይ፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ ነህ፤

ለሚጠሩህ ሁሉ ምሕረትህ ወሰን የለውም።

6 እግዚአብሔርሆይ፤ ጸሎቴን አድምጥ፤

የልመናዬን ጩኸት ስማ።

7 አንተ ስለምትመልስልኝ፣

በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጣራለሁ።

8 ጌታ ሆይ፤ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ የለም፤

ከአንተም ሥራ ጋር የሚወዳደር ሥራ የለም።

9 ጌታ ሆይ፤ አንተ የሠራሃቸው ሕዝቦች ሁሉ፣

መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ፤

ለስምህም ክብር ይሰጣሉ፤

10 አንተ ታላቅ ነህና፤ ታምራትም ትሠራለህ፤

አንተ ብቻህን አምላክ ነህ።

11 እግዚአብሔርሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤

በእውነትህም እሄዳለሁ፤

ስምህን እፈራ ዘንድ፣

ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ።

12 ጌታ አምላኬ ሆይ፤ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤

ስምህንም ለዘላለም አከብራለሁ፤

13 ለእኔ ያሳየሃት ምሕረት ታላቅ ናትና፤

ነፍሴንም ከሲኦልጥልቀት አውጥተሃል።

14 አምላክ ሆይ፤ እብሪተኞች ተነሥተውብኛል፤

የዐመፀኞችም ጉባኤ ነፍሴን ይሿታል፤

አንተንም ከምንም አልቈጠሩም።

15 ጌታ ሆይ፤ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ፤

ለቊጣ የዘገየህ፣ ምሕረትህና ታማኝነትህ የበዛ።

16 ወደ እኔ ተመልከት፤ ማረኝም፤

ለባሪያህ ኀይልህን ስጥ፤

የሴት ባሪያህንምልጅ አድን።

17 የሚጠሉኝ አይተው ያፍሩ ዘንድ፣

የበጎነትህን ምልክት አሳየኝ፤

እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ ረድተኸኛልና፤ አጽናንተኸኛልም።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *