መዝሙርና ለእግዚአብሔር ታማኝነት የቀረበ ጸሎት
የይዝራኤላዊው የኤታን ትምህርት
1 ስለእግዚአብሔርምሕረት ለዘለላለም እዘምራለሁ፤
በአፌም ታማኝነትህን ከትውልድ እስከ ትውልድ እገልጻለሁ።
2 ምሕረትህን ለዘላለም እንደምትመሠርት፣
ታማኝነትህንም በሰማይ እንደምታጸና እናገራለሁና።
3 አንተም እንዲህ ብለሃል፤ “ከመረጥሁት ጋር ኪዳን ገብቻለሁ፤
ለባሪያዬ ለዳዊት ምያለሁ፤
4 ‘ዘርህን ለዘላለም እተክላለሁ፤
ዙፋንህንም ከትውልድ እስከ ትውልድ አጸናለሁ።’ ”ሴላ
5 እግዚአብሔርሆይ፤ ሰማያት ድንቅ ሥራህን፣
ታማኝነትህንም በቅዱሳን ጉባኤ መካከል ያወድሳሉ፤
6 በላይ በሰማያትከእግዚአብሔርጋር ማን ሊስተካከል ይችላል?
ከሰማያውያን ፍጥረታትስ መካከል ማንእግዚአብሔርንይመስለዋል?
7 እግዚአብሔር በቅዱሳን ጉባኤ መካከል በጣም የሚፈራ፣
በዙሪያውም ካሉት ሁሉ በላይ እጅግ የሚከበር ነው።
8 የሰራዊት አምላክእግዚአብሔርሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ ኀያል ነህ፤ ታማኝነትህም ከብቦሃል።
9 የባሕርን ቍጣ ትቈጣጠራለህ፤
ሞገዱም ሲነሣ ጸጥ ታደርገዋለህ።
10 አንተ ረዓብን የተሰየፈ ያህል አደቀቅኸው፤
በብርቱ ክንድህም ጠላቶችህን በተንሃቸው።
11 ሰማያት የአንተ ናቸው፤ ምድርም የአንተ ናት፤
ዓለምንና በውስጧ ያለውን ሁሉ አንተ መሠረትህ።
12 ሰሜንንና ደቡብን የፈጠርህ አንተ ነህ፤
ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ሐሤት ያደርጋሉ።
13 አንተ ክንደ ብርቱ ነህ፤
እጅህ ኀያል ናት፤ ቀኝ እጅህም ከፍ ከፍ ያለች ናት።
14 ጽድቅና ፍትሕ የዙፋንህ መሠረቶች ናቸው፤
ምሕረትና ታማኝነት በፊትህ ይሄዳሉ።
15 እግዚአብሔርሆይ፤ እልልታን የሚያውቅ፣
በፊትህም ብርሃን የሚሄድ ሕዝብ ምስጉን ነው።
16 ቀኑን ሙሉ በስምህ ደስ ይላቸዋል፤
በጽድቅህም ሐሤት ያደርጋሉ፤
17 አንተ የብርታታቸው ክብር ነህና፤
በሞገስህም ቀንዳችንንከፍ ከፍ አደረግህ።
18 ጋሻችንየእግዚአብሔርነውና፤
ንጉሣችንም የራሱ የእስራኤል ቅዱስ ነው።
19 በዚያን ጊዜ በራእይ ተናገርህ፤
ታማኝ ሕዝብህንም እንዲህ አልህ፤
“ኀያሉን ሰው ሥልጣን አጐናጸፍሁት፤
ከሕዝብ መካከል የተመረጠውንም ከፍ ከፍ አደረግሁት።
20 ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፤
በተቀደሰው ዘይቴም ቀባሁት።
21 እጄ ይደግፈዋል፤
ክንዴም ያበረታዋል።
22 በጠላት አይበለጥም፤
ክፉ ሰውም አይበግረውም።
23 ባላንጣዎቹን በፊቱ አደቅቃቸዋለሁ፤
ጠላቶቹንም እቀጠቅጣለሁ።
24 ታማኝነቴና ምሕረቴ ከእርሱ
ጋር ይሆናል፤
በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል።
25 እጁን በባሕር ላይ፣
ቀኝ እጁንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ።
26 እርሱም፣ ‘አንተ አባቴ ነህ፤
አምላኬና መዳኛ ዐለቴም ነህ’ ብሎ ይጠራኛል።
27 እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፤
ከምድር ነገሥታትም በላይ ከፍ ይላል።
28 ምሕረቴንም ለዘላለም ለእርሱ እጠብቃለሁ፤
ከእርሱ ጋር የገባሁት ኪዳንም ጸንቶ ይኖራል።
29 የዘር ሐረጉን ለዘላለም፣
ዙፋኑንም በሰማያት ዕድሜ ልክ አጸናለሁ።
30 “ልጆቹ ሕጌን ቢተዉ፣
ደንቤን ባይጠብቁ፣
31 ሥርዐቴን ቢጥሱ፣
ትእዛዜንም ባያከብሩ፣
32 ኀጢአታቸውን በበትር፣
በደላቸውን በጅራፍ እቀጣለሁ።
33 ምሕረቴን ግን ከእርሱ አላርቅም፤
ታማኝነቴንም አላጓድልበትም።
34 ኪዳኔን አላፈርስም፤
ከአፌ የወጣውንም አላጥፍም።
35 አንድ ጊዜ በቅድስናዬ ምያለሁና፣
ዳዊትን አልዋሸውም።
36 የዘር ሐረጉ ለዘላለም፣
ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሓይ ጸንቶ ይኖራል፤
37 በሰማይ ታማኝ ምስክር ሆና እንደምትኖረው፣
እንደ ጨረቃ እርሱ ለዘላለም ይመሠረታል።”ሴላ
38 አሁን ግን ናቅኸው፤ ጣልኸውም፤
የቀባኸውንም እጅግ ተቈጣኸው።
39 ከባሪያህ ጋር የገባኸውን ኪዳን አፈረስህ፤
የክብር ዘውዱን ትቢያ ላይ ጥለህ አቃለልኸው።
40 ቅጥሩን ሁሉ አፈራረስህ፤
ምሽጉንም ደመሰስህ።
41 ዐላፊ አግዳሚው ሁሉ ዘረፈው፤
ለጎረቤቶቹ መዘባበቻ ሆነ።
42 የጠላቶቹን ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አደረግህ፤
ባላንጣዎቹም ሁሉ ደስ አላቸው።
43 የሰይፉን ስለት አጠፍህ፤
በጦርነትም ጊዜ አልረዳኸውም።
44 ግርማዊነቱን አጠፋህበት፤
ዙፋኑንም ከዐፈር ደባለቅኸው።
45 የወጣትነት ዘመኑን አሳጠርኸው፤
ዕፍረትንም አከናነብኸው።ሴላ
46 እግዚአብሔርሆይ፤ ይህ እስከ መቼ ይሆናል? ራስህንስ ለዘላለም ትሰውራለህን?
ቍጣህስ እንደ እሳት የሚነደው እስከ መቼ ነው?
47 ዘመኔ ምን ያህል አጭር እንደሆነች አስብ፤
የሰውን ልጆች እንዲያው ለከንቱ ፈጠርሃቸው!
48 ሞትን ሳያይ ሕያው ሆኖ የሚቀር
ሰው አለን?
ራሱን ከሲኦል እጅ ማዳን የሚችል ማን ነው?ሴላ
49 ጌታ ሆይ፤ ለዳዊት በታማኝነትህ የማልህለት፣
የቀድሞው ምሕረትህ የት አለ?
50 ጌታ ሆይ፤ ባሪያህእንዴት እንደ ተፌዘበት፣
የብዙ ሰዎችንም ነቀፋ እንደ ታቀፍሁ አስብ።
51 እግዚአብሔርሆይ፤ ጠላቶችህ የተሣለቁበትን፣
የቀባኸውን ሰው እርምጃ የነቀፉበትን ሁኔታ አስብ።
52 እግዚአብሔርለዘላለም ይባረክ፤
አሜን፤ አሜን።