የየዕለቱ መዝሙር
1 ኑ፤ ደስ እያለንለእግዚአብሔርእንዘምር፤
በድነታችንም ዐለት እልል እንበል።
2 ምስጋና ይዘን ፊቱ እንቅረብ፤
በዝማሬም እናወድሰው።
3 እግዚአብሔርታላቅ አምላክ ነውና፤
ከአማልክትም ሁሉ በላይ ታላቅ ንጉሥ ነው።
4 የምድር ጥልቆች በእጁ ናቸው፤
የተራራ ጫፎችም የእርሱ ናቸው።
5 እርሱ ፈጥሮአታልና፣ ባሕር የእርሱ ናት፤ እጁም የብስን አበጀ።
6 ኑ፤ እናምልከው፤ እንስገድለትም፤
በፈጣሪያችንበእግዚአብሔርፊት እንንበርከክ፤
7 እርሱ አምላካችን ነውና፤
እኛም በእጁ ጥበቃ ሥር ያለን በጎቹ፣
የመሰማሪያውም ሕዝብ ነን።
ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣
8 በምድረ በዳ በነበራችሁበት ቀን በማሳህ፣
በመሪባምእንዳደረጋችሁት፣ ልባችሁን አታደንድኑ።
9 ሥራዬን ቢያዩም፣
አባቶቻችሁ በዚያ ፈተኑኝ፤ ተፈታተኑኝም።
10 ያን ትውልድ አርባ ዓመት ሙሉ ተቈጣሁት፤
እኔም፣ “ልቡ የሸፈተ ሕዝብ ነው፤
መንገዴንም አላወቀም” አልሁ።
11 ስለዚህ፣ “ፈጽሞ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም” ብዬ፣
በቍጣዬ ማልሁ።