ትንቢተ ሚልክያስ
1 በሚልክያስበኩል ወደ እስራኤል የመጣውየእግዚአብሔርቃል ንግር ይህ ነው፤
ያዕቆብ ተወደደ፤ ዔሳው ተጠላ
2 “እኔ ወድጃችኋለሁ” ይላልእግዚአብሔር፤“እናንተ ግን፣ ‘እንዴት ወደድኸን?’ ትላላችሁ።
እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ያዕቆብን ወደድሁት፤
3 ዔሳውን ግን ጠላሁት፤ ተራሮቹን ባድማ አደረግሁ፤ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮዎች ሰጠሁበት።”
4 ኤዶምያስ፣ “ብንደመሰስም እንኳ የፈረሰውን መልሰን እንሠራዋለን” ይል ይሆናል።እግዚአብሔርጸባኦት ግን እንዲህ ይላል፤ “እነርሱ ይሠሩ ይሆናል፤ እኔ ግን አፈርስባቸዋለሁ፤ ክፉ ምድር፣እግዚአብሔርምለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ተብለው ይጠራሉ።
5 ይህንም በገዛ ዐይናችሁ ታያላችሁ፤ እናንተም፣ ‘ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ እንኳእግዚአብሔርታላቅ ነው!’ ትላላችሁ።
እንከን ያለበት መሥዋዕት
6 “ልጅ አባቱን፣ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔ አባት ከሆንሁ፣ መከበሬ የት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ የት አለ?” ይላልእግዚአብሔርጸባኦት፤ ካህናት ሆይ፤ ስሜን የምታቃልሉት እናንተ ናችሁ።
“እናንተ ግን፣ ‘ስምህን ያቃለልነው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ።
7 “በመሠዊያዬ ላይ የረከሰ ምግብ ታስቀምጣላችሁ።
“እናንተ ግን፣ ‘ያረከስንህ እንዴት ነው?’ አላችሁ።
“የእግዚአብሔርገበታ የተናቀ ነው በማለታችሁ ነው።
8 የታወረውን እንስሳ ለመሥዋዕት ስታቀርቡ፣ ያ በደል አይደለምን? አንካሳውን ወይም በሽተኛውን እንስሳ መሥዋዕት አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ያስ በደል አይደለምን? ያንኑ ለገዣችሁ ብታቀርቡ፣ በእናንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ይቀበለዋልን?” ይላልእግዚአብሔርጸባኦት።
9 “አሁን ግን እንዲራራልን እግዚአብሔርን ለምኑ፤ እንደዚህ ዐይነቱን መሥዋዕት ይዛችሁ ስትቀርቡ ይቀበላችኋልን?” ይላልእግዚአብሔርጸባኦት።
10 “በመሠዊያዬ ላይ ከንቱ እሳት እንዳታነዱ፣ ምነው ከእናንተ አንዱ የቤተ መቅደሱን ደጅ በዘጋ ኖሮ! እኔ በእናንተ ደስ አይለኝም፤ ከእጃችሁም ምንም ዐይነት ቊርባን አልቀበልም’ ይላልእግዚአብሔርጸባኦት።
11 ከፀሓይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ፣ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናል፤ በየስፍራውም ሁሉ ለስሜ ዕጣንና ንጹሕ ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናልና” ይላልእግዚአብሔርጸባኦት።
12 “እናንተ ግን የእግዚአብሔር ገበታ፣ ‘ርኩስ ነው’ ምግቡም፣ ‘የተናቀ ነው’ በማለት ታቃልላላችሁ።
13 ደግሞም፣ ‘ይህ ድካም ነው’ በማለት በንቀት ጢቅ አላችሁበት ይላልእግዚአብሔርጸባኦት።
“በቅሚያ የመጣውን፣ አንካሳውንና የታመመውን እንስሳ ቊርባን አድርጋችሁ ስታቀርቡ ከእጃችሁ መቀበል ይገባኛልን?” ይላልእግዚአብሔር፤
14 “በመንጋው ውስጥ ተቀባይነት ያለው ተባዕት በግ ኖሮት ይህንኑ ሊሰጥ ተስሎ ሳለ በማታለል ነውር ያለበትን እንስሳ ለጌታ የሚሠዋ ርጒም ይሁን፤ እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝ፤ ስሜም በሕዝቦች ዘንድ ሊፈራ የሚገባ ነውና” ይላልእግዚአብሔርጸባኦት።