የእግዚአብሔርና የሰው ዕቅድ
1 ክፉ ለመሥራት ለሚያቅዱ፣
በመኝታቸው ሳሉ ተንኰል ለሚያውጠነጥኑ ወዮላቸው!
ሲነጋ በማለዳ ይፈጽሙታል፤
የሚያደርጉበት ኀይል በእጃቸው ነውና።
2 ዕርሻ ይመኛሉ፤ ይይዙታልም፤
ቤት ይመኛሉ፤ ይወስዱታልም፤
የሰውን ቤት፣
የባልንጀራን ርስት አታልለው ይወስዳሉ።
3 ስለዚህእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ በዚያ ሕዝብ ላይ ጥፋት ላመጣ ዐቅጃለሁ፤
ከዚህም ለማምለጥ አትችሉም።
ከእንግዲህ በትዕቢት አትመላለሱም፤
የመከራ ጊዜ ይሆናልና።
4 በዚያ ቀን ሰዎች ይሣለቁባችኋል፤
በሐዘን እንጒርጒሮ እንዲህ እያሉ ያፌዙባችኋል፤
‘እኛ ፈጽሞ ጠፍተናል፤
የወገኔ ርስት ተከፋፍሎአል።
ከእኔ ነጥቆ ወስዶ፣
ዕርሻዎቻችንን ላሸነፉን አከፋፈለ።’
5 ስለዚህበእግዚአብሔርጉባኤ ውስጥ፣
መሬት በዕጣ የሚያካፍል ማንም አይኖርም።
ሐሰተኞች ነቢያት
6 ነቢያቶቻቸው፣ “ትንቢት አትናገርብን፤
ስለ እነዚህ ነገሮች ትንቢት አትናገር፤
ውርደት አይደርስብንም” ይላሉ።
7 የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ እንዲህ ሊባል ይገባልን?
“የእግዚአብሔርመንፈስ የማይታገሥ ነውን?
እንዲህ ያሉት ነገሮችንስ ያደርጋልን?”
“መንገዱ ቀና ለሆነ፣
ቃሌ መልካም አያደርግምን?
8 በመጨረሻ በሕዝቤ ላይ ጠላት ሆናችሁ
ተነሣችሁ፤
የጦርነት ሐሳብ ሳይኖራቸው፣
በሰላም ከሚያልፉ ሰዎች ላይ፣
ማለፊያ መጐናጸፊያ ገፈፋችሁ።
9 ከሚወዱት ቤታቸው፣
የሕዝቤን ሴቶች አስወጣችኋቸው፤
ክብሬን ከልጆቻቸው፣
ለዘላለም ወሰዳችሁ።
10 ተነሡና፤ ከዚያ ሂዱ፤
ይህ ማረፊያ ቦታችሁ አይደለምና፤
ምክንያቱም ረክሶአል፤
ክፉኛም ተበላሽቶአል።
11 ሐሰተኛና አታላይ ሰው መጥቶ፣
‘ስለ ብዙ የወይን ጠጅና ስለሚያሰክር መጠጥ ትንቢት እነግራችኋለሁ’ ቢል፣
ለዚህ ሕዝብ ተቀባይነት ያለው ነቢይ ይሆናል።
የትድግና ተስፋ
12 “ያዕቆብ ሆይ፤ በእርግጥ ሁላችሁንም እሰበስባለሁ፤
የእስራኤልንም ትሩፍ በአንድነት አመጣለሁ፤
በጒረኖ ውስጥ እንዳሉ በጎች በመሰማሪያ ላይ እንዳለ መንጋ በአንድነት
እሰበስባቸዋለሁ፤
ቦታውም በሕዝብ ይሞላል።
13 የሚሰብረው ወጥቶ በፊታቸው ይሄዳል፤
እነርሱም በሩን በመስበር ወጥተው ይሄዳሉ፤
እግዚአብሔርእየመራቸው፣
ንጉሣቸው ቀድሞአቸው ይሄዳል።