ሚክያስ 3

መሪዎችና ነቢያት ተገሠጹ

1 ከዚያም እኔ እንዲህ አልሁ፤

“እናንት የያዕቆብ መሪዎች፤

እናንት የእስራኤል ቤት ገዦች ስሙ፤

ፍትሕን ማወቅ አይገባችሁምን?

2 መልካሙን ጠላችሁ፤ ክፉውንም ወደዳችሁ፤

የሕዝቤን ቈዳ ገፈፋችሁ፤

ሥጋቸውንም ከዐጥንቶቻቸው ለያችሁ፤

3 የሕዝቤን ሥጋ በላችሁ፤

ቈዳቸውን ገፈፋችሁ፤

ዐጥንቶቻቸውንም ሰባበራችሁ፤

በመጥበሻ እንደሚጠበስ፣

በድስት እንደሚቀቀል ሥጋ ቈራረጣችኋቸው።

4 እነርሱም ወደእግዚአብሔርይጮኻሉ፤

እርሱ ግን አይመልስላቸውም፤

ካደረጉት ክፋት የተነሣ፣

በዚያ ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።

5 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“ሕዝቤን የሚያስቱ ነቢያት፣

ሰው ሲያበላቸው፣ ‘ሰላም አለ’ ይላሉ፤

ሳያበላቸው ሲቀር ግን፣

ጦርነት ሊያውጁበት ይነሣሉ።

6 ስለዚህ ሌሊቱ ያለ ራእይ፣

ጨለማውም ያለ ንግርት ይመጣባችኋል፤

በነቢያት ላይ ፀሐይ ትጠልቅባቸዋለች፤

ቀኑም ይጨልምባቸዋል።

7 ባለ ራእዮች ያፍራሉ፤

ንግርተኞችም ይዋረዳሉ፤

ሁሉም ፊታቸውን ይሸፍናሉ፤

ከእግዚአብሔር መልስ የለምና።”

8 እኔ ግን፣

ለያዕቆብ በደሉን፣

ለእስራኤልም ኀጢአቱን እነግር ዘንድ

ኀይልን፣በእግዚአብሔርመንፈስ፣

ፍትሕና ብርታት ተሞልቻለሁ።

9 እናንት የያዕቆብ ቤት መሪዎች፣

እናንት የእስራኤል ቤት ገዦች፣

ፍትሕን የምትንቁ፤

ትክክለኛ የሆነውንም ነገር ሁሉ የምታጣምሙ፤ ስሙ፤

10 ጽዮንን ደም በማፍሰስ፣

ኢየሩሳሌምን በክፋት የምትገነቡ፤ ስሙ።

11 መሪዎቿ በጒቦ ይፈርዳሉ፤

ካህናቷ ለዋጋ ሲሉ ያስተምራሉ፤

ነቢያቷም ለገንዘብ ሲሉ ይናገራሉ።

ነገር ግንበእግዚአብሔርላይ ተደግፈውም፣

“እግዚአብሔርበመካከላችን አይደለምን?

ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም” ይላሉ።

12 ስለዚህ በእናንተ ምክንያት፣

ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፣

ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤

የቤተ መቅደሱም ኰረብታ ዐረም የበቀለበት ጒብታ ይሆናል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *