የእግዚአብሔር ተራራ
1 በመጨረሻው ዘመን፣
የእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ተራራ፣
ከተራሮች ልቆ ይታያል፤
ከኰረብቶች በላይ ከፍ ይላል፤
ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።
2 ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤
“ኑ፤ ወደእግዚአብሔርተራራ፣
ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንሂድ፤
በመንገዱ እንድንሄድ፣
መንገዱን ያስተምረናል።”
ሕግ ከጽዮን ይመጣል፤
የእግዚአብሔርምቃል ከኢየሩሳሌም።
3 እርሱ በብዙ ሕዝብ መካከል ይፈርዳል፤
በሩቅና በቅርብ ባሉ ኀያላን መንግሥታት መካከል ያለውን ግጭት ያቆማል፤
ሰይፋቸውን ማረሻ፣
ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል።
አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤
ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም።
4 እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣
ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤
የሚያስፈራቸው አይኖርም፤
የእግዚአብሔርጸባኦት አፍ ተናግሮአልና።
5 አሕዛብ ሁሉ፣
በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤
እኛ ግንበአምላካችንበእግዚአብሔር ስም፣
ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።
የእግዚአብሔር ዕቅድ
6 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“በዚያች ቀን ሽባውን እሰበስባለሁ፤
ስደተኞችንና ለሐዘን ያደረግኋቸውን፣
ወደ አንድ ቦታ አመጣለሁ።
7 የሽባዎችን ትሩፍ፣
የተገፉትንም ብርቱ ሕዝብ አደርጋለሁ፤
ከዚያች ቀን አንሥቶ እስከ ዘላለም፣
እግዚአብሔርበጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።
8 አንተ የመንጋው መጠበቂያ ማማ ሆይ፤
የጽዮን ሴት ልጅ ዐምባሆይ፤
የቀድሞው ግዛትህ ይመለስልሃል፤
የመንግሥትም ሥልጣን ለኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ይሆናል።”
9 አሁንስ እንደዚህ የምትጮኺው ለምንድን ነው?
ንጉሥ የለሽምን?
ምጥ እንደ ያዛት ሴት የተጨነቅሽው፣
መካሪሽ ስለ ጠፋ ነውን?
10 የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፤
ምጥ እንደ ያዛት ሴት ተጨነቂ፤
አሁንስ ከከተማ ወጥተሽ፣
በሜዳ ላይ መስፈር አለብሽና፤
ወደ ባቢሎን ትሄጃለሽ፣
በዚያ ከጠላት እጅ ትድኛለሽ፤
እግዚአብሔርበዚያ፣
ከጠላቶችሽ ይታደግሻል።
11 አሁን ግን ብዙ አሕዛብ፣
በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል፤
እነርሱም፣ “የረከሰች ትሁን፤
ዐይናችንም ጽዮንን መዘባበቻ አድርጎ ይያት” ይላሉ።
12 ነገር ግንየእግዚአብሔርንሐሳብ አያውቁም፤
በአውድማ ላይ እንደ ነዶ
የሚሰበስባቸውን፣
የእርሱን ዕቅድ አያስተውሉም።
13 የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ተነሥተሽ አበራዪ፤
የብረት ቀንድ እሰጥሻለሁና፤
የናስ ሰኰና እሰጥሻለሁ፤
አሕዛብንም ታደቂያቸዋለሽ።”
በግፍ ያግበሰበሱትን ትርፍለእግዚአብሔር፣
ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ ታቀርቢያለሽ።