የእግዚአብሔር ክስ በእስራኤልን ላይ
1 እግዚአብሔርየሚለውን ስሙ፤
“ተነሡ፤ ጒዳያችሁን በተራሮችም፤
ፊት አቅርቡ፤
ኰረብቶች እናንተ የምትሉትን ይስሙ፤
2 ተራሮች ሆይ፤የእግዚአብሔርንክስ አድምጡ፤
እናንት የምድር ጽኑ መሠረቶችም፤ ስሙ፤
እግዚአብሔርከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፤
ከእስራኤልም ጋር ይፋረዳል።
3 “ሕዝቤ ሆይ፤ ምን አድርጌሃለሁ?
ሸክም የሆንሁብህስ እንዴት ነው?
እስቲ መልስልኝ!
4 ከግብፅ አወጣሁህ፤
ከባርነት ምድርም ተቤዠሁህ፤
እንዲመሩህ ሙሴን፣
አሮንንና ማርያምን ላክሁልህ።
5 ሕዝቤ ሆይ፤
የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ የመከረውን፣
የቢዖር ልጅ በለዓም የመለሰለትንም እስቲ አስቡ፤
የእግዚአብሔርንየጽድቅ ሥራ ታውቁ ዘንድ፣
ከሰጢም እስከ ጌልገላ የተጓዛችሁትን አስቡ።
6 ምን ይዤበእግዚአብሔርፊት ልቅረብ፣
በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ?
የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣
ከአንድ ዓመት ጥጃ ጋር ይዤ በፊቱ ልቅረብን?
7 በአንድ ሺህ አውራ በጎች፣
በዐሥር ሺህ የዘይት ፈሳሽእግዚአብሔርደስ ይለዋልን?
ስለ በደሌ የበኵር ልጄን፣
ስለ ነፍሴም ኀጢአት የሆዴን ፍሬ ላቅርብለትን?
8 ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤
እግዚአብሔርከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?
ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣
በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?
የእስራኤል በደልና ቅጣት
9 ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤
ስሙ!እግዚአብሔርከተማዪቱን እንዲህ እያለ ይጣራል፤
“በትሩን አስቡ፤ ያዘጋጀውም ማን እንደሆነ አስታውሱ።
10 የክፋት ቤት ሆይ፤
በግፍ የተገኘ ሀብታችሁን፣
በሐሰተኛ መስፈሪያ የሰበሰባችሁትን አስጸያፊ ነገር እረሳዋለሁን?
11 አባይ ሚዛን የያዘውን ሰው፣
ሐሰተኛ መመዘኛ በከረጢት የቋጠረውን ንጹሕ ላድርገውን?
12 ባለጠጎቿ ግፈኞች፣
ሰዎችዋ ሐሰተኞች ናቸው፤
ምላሳቸውም አታላይ ናት።
13 ስለዚህ አንተን አጠፋሃለሁ፣
ከኀጢአትህ የተነሣ አፈራርስሃለሁ።
14 ትበላለህ፤ ነገር ግን አትጠግብም፤
ሆድህ እንዳለ ባዶውንይቀራል፤
ታከማቻለህ፤ ነገር ግን አይጠራቀምልህም፤
የሰበሰብኸውን ለሰይፍ አደርገዋለሁና።
15 ትዘራለህ፤ ነገር ግን አታጭድም፤
የወይራ ዘይት ትጨምቃለህ፤ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤
ወይንን ትቈርጣለህ፤ ነገር ግን የወይን ጠጅ አትጠጣም።
16 የዖምሪን ሥርዐት፣
የአክዓብን ቤት ልምድ ሁሉ የሙጥኝ ብለሃል፤
ትውፊታቸውንም ተከትለሃል።
ስለዚህ አንተን ለውድመት፣
ሕዝብህን ለመዘባበቻ አሳልፌ እሰጣለሁ፤
አሕዛብም ይሣለቁብሃል።”