ማሕልየ መሓልይ 1

1 ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር።

2 በከንፈሩ መሳም ይሳመኝ

ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ደስ ያሰኛልና።

3 የሽቱህ መዐዛ ደስ ያሰኛል፤

ስምህ እንደሚፈስ ሽቱ ነው፤

ታዲያ ቈነጃጅት ቢወዱህ ምን ያስደንቃል

4 ይዘኸኝ ሂድ፤ እንፍጠን፤

ንጉሡ ወደ ዕልፍኞቹ አምጥቶኛል።

በአንተደስ ይለናል፤ ሐሤትም እናደርጋለን፤

ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እንወድሳለን።

አንተን እንደዚህ ማፍቀራቸው ትክክል ነው።

5 እናንት የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፤

እኔ ጥቊር ነኝ፤ ይሁን እንጂ ውብ ነኝ፤

ጥቊረቴ እንደ ቄዳር ድንኳኖች፣

እንደ ሰሎሞንቤተ መንግሥት መጋረጃዎችም ነው።

6 ጥቊር ስለ ሆንሁ ትኵር ብላችሁ አትዩኝ፤

መልኬን ያጠቈረው ፀሓይ ነውና፤

የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ተቈጡኝ፤

የወይን ተክል ቦታዎችም ጠባቂ አደረጉኝ፤

የራሴን የወይን ተክል ቦታ ተውሁት።

7 ውዴ ሆይ፤ መንጋህን የት እንደምታሰማራ፣

በቀትርም የት እንደምትመስጋቸው

እባክህ ንገረኝ፤

በወዳጆችህ መንጎች ኋላ፣

ፊቷን ሸፍና እንደምትቅበዘበዝ ሴት ለምን ልሁን?

8 አንቺ ከሴቶች ሁሉ ይበልጥ የተዋብሽ ሆይ፤ የማታውቂ ከሆነ፣

የበጎቹን ዱካ ተከተዪ፤

የፍየል ግልገሎችሽንም፣

በእረኞቹ ድንኳን አጠገብ አሰማሪ።

9 ውዴ ሆይ፤ የፈርዖንን ሠረገሎች ከሚስቡ ፈረሶች መካከል፣

በአንዲቱ ባዝራ መሰልሁሽ።

10 ጒንጮችሽ በጒትቻ፣

ዐንገትሽም በዕንቊ ሐብል አጊጠዋል።

11 እኛም ባለ ብር ፈርጥ፣

የወርቅ ጒትቻ እናሠራልሻለን።

12 ንጉሡ ማእዱ ላይ ሳለ፣

ሽቱዬ መዐዛውን ናኘው።

13 ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንዳረፈ፣

በመቋጠሪያ እንዳለ ከርቤ ነው።

14 ውዴ ለእኔ ከዓይንጋዲ የወይን ተክል ቦታ፣

እንደ መጣ የሄና አበባ ዕቅፍ ነው።

15 ውዴ ሆይ፤ እንዴት ውብ ነሽ

እንዴትስ ያለሽ ቈንጆ ነሽ

ዐይኖችሽም እንደ ርግብ ዐይኖች ናቸው።

16 አንተ ውዴ ሆይ፤ እንዴት ውብ ነህ

እንዴትስ ታምራለህ

ዐልጋችንም እንደ ለምለም ሣር ነው።

17 የቤታችን ተሻካሚዎች ዝግባዎች፣

የጣራችን ማዋቀሪያዎችም ጥዶች ናቸው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *