ማሕልየ መሓልይ 7

1 አንቺ የልዑል ልጅ ሆይ፤

ነጠላ ጫማ የተጫሙ እግሮችሽ

እንዴት ያምራሉ ሞገስን የተጐናጸፉ ዳሌዎችሽ፣

ብልኅ አንጥረኛ የተጠበባቸውን የዕንቊ ሐብል ይመስላሉ።

2 ዕንብርትሽ ጥሩ የወይን ጠጅ እንደ ማይጐድልበት፣

እንደ ክብ ጽዋ ነው፤

ወገብሽ ዙሪያውን በውብ አበባ የታሰረ

የስንዴ ክምር ይመስላል።

3 ሁለት ጡቶችሽ፣

መንታ የዋልያ ግልገሎችን ይመስላሉ።

4 ዐንገትሽ በዝሆን ጥርስ እንዳጌጠ መጠበቂያ ማማ ነው፤

ዐይኖችሽ በባትረቢ በር አጠገብ እንዳሉት፣

እንደ ሐሴቦን ኵሬዎች ናቸው፤

አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አቅጣጫ እንደሚመለከት፣

እንደ ሊባኖስ መጠበቂያ ማማ ነው።

5 የራስሽ ቅርጽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ አክሊል ሆኖልሻል፤

ጠጒርሽ የሐር ጒንጒን የመሰለ ነው፤

ንጉሡም በሹሩባሽ ታስሮ ተይዞአል።

6 እንዴት ውብ ነሽ! እንዴትስ ደስ የምትይ ነሽ!

ፍቅሬ ሆይ፤ የምታስደስቺ ነሽ።

7 ቁመናሽ እንደ ዘንባባ ዛፍ መለል ያለ ነው፤

ጡቶችሽም የፍሬውን ዘለላ ይመስላሉ።

8 እኔም፣ “የዘንባባውን ዛፍ እወጣለሁ፤

ዘለላዎቹንም እይዛለሁ” አልሁ።

ጡቶችሽ የወይን ዘለላ፣

የእስትንፋስሽም መዐዛ እንደ እንኰይ ፍሬ ይሁኑ፤

9 ከናፍሮችሽም እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ይጣፍጡ።

የወይን ጠጁ በቀስታ እየተንቈረቈረ፣

ወደ ውዴ ከንፈሮችና ጥርሶች ይውረድ።

10 እኔ የውዴ ነኝ፤

የእርሱም ምኞት እኔው ነኝ።

11 ውዴ ሆይ፤ ና ወደ ገጠር እንሂድ፤

ወደ መንደርምገብተን እንደር፤

12 ማልደን ወደ ወይኑ ተክል ቦታ እንሂድ፣

ወይኑ እንቡጥ አውጥቶ፣

አበባው ፈክቶ፣

ሮማኑ አፍርቶ እንደሆነ እንይ፤

በዚያም ራሴን በፍቅር እሰጥሃለሁ።

13 ትርንጐዎች መዐዛቸውን ሰጡ፤

አዲስ የተቀጠፈውም ሆነ የበሰለው፣

ጣፋጩ ፍሬ ሁሉ በደጃፋችን አለ፤

ውዴ ሆይ፤ ለአንተ አስቀምጬልሃለሁ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *