1 ምነው አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ፣
እንደ ወንድሜ በሆንህ!
ከዚያም ውጭ ባገኝህ፣
እስምህ ነበር፤
ታዲያ ማንም ባልናቀኝ!
2 እኔም ወደ አስተማረችኝ፣
ወደ እናቴም ቤት፣
እጅህን ይዤ በወሰድሁህ ነበር፤
የምትጠጣውን ጣፋጭ የወይን ጠጅ፣
የሮማኔን ጭማቂም በሰጠሁህ።
3 ግራ እጁን ተንተርሻለሁ፤
ቀኝ እጁም ዐቅፎኛል።
4 እናንት የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት፤
ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣
ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት እማጠናችኋለሁ።
5 ውዷን ተደግፋ፣
ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት?
ከእንኰይ ዛፍ ሥር አስነሣሁህ፤ በዚያ እናትህ ፀነሰችህ፤
በዚያም ታምጥ የነበረችው አንተን
ወለደችህ።
6 በልብህ እንዳለ፣
በክንድህም እንደምትይዘው ማኅተም አስቀምጠኝ፤
ፍቅር እንደ ሞት የበረታች፣
ቅናቷምእንደ መቃብርጨካኝ ናትና፤
እንደሚንቦገቦግ እሳት፣
እንደ ኀይለኛም ነበልባል ትነዳለች።
7 የውሃ ብዛት ፍቅርን ሊያጠፋ አይችልም፣
ፈሳሾችም አያሰጥሟትም፤
ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ
ስለ ፍቅር ቢሰጥ
ፈጽሞ ይናቃል።
8 ትንሽ እኅት አለችን፤
ጡትም ገና አላወጣችም፤
ስለ እርሷ በምንጠየቅበት ቀን
ምን ማድረግ እንችል ይሆን?
9 እርሷ ቅጥር ብትሆን፣
በላይዋ የብር መጠበቂያ ማማ እንሠራባታለን፤
በር ብትሆን፣
በዝግባ ዕንጨት እንከልላታለን።
10 እነሆ እኔ ቅጥር ነኝ፤
ጡቶቼም እንደ ማማ ግንቦች ናቸው፤
እኔም በዐይኖቹ ፊት፣
ሰላምን እንደሚያመጣ ሰው ሆንሁ።
11 ሰሎሞን በብኤላሞን የወይን ተክል ቦታ ነበረው፤
የወይኑን ተክል ቦታም ለአትክልተኞች አከራየው፤
እያንዳንዳቸውም የፍሬውን ዋጋ፣
አንድ አንድ ሺህ ሰቅል ብር ያመጡለት ነበር።
12 የወይኔ ተክል ቦታ የራሴ፣ የግሌ ነው፤
ሰሎሞን ሆይ፤ አንድ ሺሁ ሰቅል ለአንተ፤
ፍሬውን ለሚጠብቁ ደግም ሁለት መቶ ይሁን።
13 አንቺ በአትክልቱ ቦታ የምትኖሪ ሆይ፤
ባልንጀሮቼ ድምፅሽን ይሰማሉ፤
እስቲ እኔም ልስማው።
14 ውዴ ሆይ፤ ቶሎ ናልኝ፤
ሚዳቋን፣
ወይም በቅመም ተራራ ላይ የሚዘል፣
የዋልያን ግልገል ምሰል።