ምሳሌ 16

1 የልብ ዕቅድ የሰው ነው፤

የአንደበት መልስ ግንከእግዚአብሔርዘንድ ነው።

2 ለሰው መንገዱ ሁሉ ንጹሕ መስሎ ይታየዋል፤

መነሻ ሐሳቡ ግንበእግዚአብሔርይመዘናል።

3 የምታደርገውን ሁሉለእግዚአብሔርዐደራ ስጥ፤

ዕቅድህም ሁሉ ይሳካልሃል።

4 እግዚአብሔርሁሉንም ነገር ለራሱ ዐላማ ሠርቶአል፤

ክፉዎችንም እንኳ ለጥፋት ቀን አዘጋጅቶአል።

5 እግዚአብሔርበልብ የሚታበዩትን ሁሉ ይጸየፋል፤

እነርሱም ከቅጣት እንደማያመልጡ በርግጥ ዕወቅ።

6 በፍቅርና በታማኝነት ኀጢአት ይሰረያል፤

እግዚአብሔርንበመፍራት ሰው ከክፋት ይርቃል።

7 የሰው መንገድእግዚአብሔርንደስ ሲያሰኘው፣

ጠላቶቹ እንኳ አብረውት በሰላም እንዲኖሩ ያደርጋል።

8 ከጽድቅ ጋር ጥቂቱ ነገር፣

በግፍ ከሚገኝ ብዙ ትርፍ ይሻላል።

9 ሰው በልቡ መንገዱን ያቅዳል፤

እግዚአብሔርግን ርምጃውን ይወስንለታል።

10 የንጉሥ ከንፈሮች እንደ አምላክ ቃል ይናገራሉ፤

አንደበቱ ፍትሕን ያዛባ ዘንድ አይገባም።

11 ሐቀኛ መስፈሪያና ሚዛንከእግዚአብሔርናቸው፤

በከረጢት ውስጥ ያሉት መመዘኛዎችም ሁሉ ሥራዎቹ ናቸው።

12 ክፋትን ማድረግ ለነገሥታት አጸያፊ ነው፤

ዙፋን የሚጸናው በጽድቅ ነውና።

13 ነገሥታት በታማኝ ከንፈሮች ደስ ይላቸዋል፤

እውነት የሚናገረውን ሰው ይወዱታል።

14 የንጉሥ ቊጣ የሞት መልእክተኛ ነው፤

ጠቢብ ሰው ግን ቊጣውን ያበርዳል።

15 የንጉሥ ፊት ሲፈካ ሕይወት አለ፤

በጎነቱም ዝናብ እንዳዘለ የበልግ ደመና ነው።

16 ከወርቅ ይልቅ ጥበብን ማግኘት፣

ከብርም ማስተዋልን መምረጥ ምንኛ ይበልጣል!

17 የቅኖች ጐዳና ከክፋት የራቀ ነው፤

መንገዱንም የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል።

18 ትዕቢት ጥፋትን፣

የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች።

19 በተዋረደ መንፈስ ከተጨቈኑት ጋር መሆን፣

ከትዕቢተኞች ጋር ብዝበዛን ከመካፈል ይሻላል።

20 ምክርን የሚሰማ ይለመልማል፤

በእግዚአብሔርምየሚታመን ቡሩክ ነው።

21 ልባቸው ጠቢብ የሆነ አስተዋዮች ይባላሉ፤

ደስ የሚያሰኙ ቃላትም ዕውቀትን ያዳብራሉ።

22 ማስተዋልን ገንዘብ ላደረጋት የሕይወት ምንጭ ናት፤

ቂልነት ግን በተላሎች ላይ ቅጣት ታመጣባቸዋለች።

23 የጠቢብ ሰው ልብ አንደበቱን ይመራል፤

ከንፈሮቹም ዕውቀትን ያዳብራሉ።

24 ደስ የሚያሰኝ ቃል የማር ወለላ ነው፤

ለነፍስ ጣፋጭ፣ ለዐጥንትም ፈውስ ነው።

25 ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤

በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል፤

26 ሠራተኛን የዕለት ጒርስ ፍላጎቱ ታታሪ ያደርገዋል፤

ራቡም ይገፋፋዋል።

27 ወራዳ ሰው ክፋትን ያውጠነጥናል፤

ንግግሩም እንደሚለበልብ እሳት ነው።

28 ጠማማ ሰው ጠብን ይዘራል፤

ሐሜተኛም የቅርብ ወዳጆችን ይለያያል።

29 ክፉ ሰው ባልንጀራውን ያባብለዋል፤

መልካም ወዳልሆነውም መንገድ ይመራዋል።

30 በዐይኑ የሚጠቅስ ሰው ጠማማነትን ያውጠነጥናል፤

በከንፈሩ የሚያሽሟጥጥም ወደ ክፋት ያዘነብላል።

31 ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤

የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው።

32 ታጋሽ ሰው ከጦረኛ፣

ስሜቱን የሚገዛም ከተማን በጒልበቱ ከሚይዝ ይበልጣል።

33 ዕጣ በጒያ ውስጥ ይጣላል፤

ውሳኔው በሙሉ ግንከእግዚአብሔርዘንድ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *