ከጥበብ የሚገኝ ተጨማሪ በረከት
1 ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤
ትእዛዛቴን በልብህ ጠብቅ፤
2 ቀኖችን ይጨምሩልሃል፤ ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤
ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል።
3 ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤
በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤
በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው።
4 በዚያን ጊዜ ሞገስንና መልካም ስምን፣
በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ።
5 በፍጹም ልብህበእግዚአብሔርታመን፤
በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤
6 በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤
እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።
7 በራስህ አስተያየት ጠቢብ ነኝ አትበል፤
እግዚአብሔርንፍራ፤ ከክፉም ራቅ።
8 ይህም ለሰውነትህ ጤንነትን፣
ለዐጥንትህም ልምላሜን ያመጣልሃል።
9 እግዚአብሔርንበሀብትህ፣
ከምርትህ ሁሉ በኵራት አክብረው፤
10 ይህን ብታደርግ፣ ጎተራህ ሞልቶ ይትረፈረፋል፤
መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ቲፍ ብሎ ይሞላል።
11 ልጄ ሆይ፤የእግዚአብሔርንተግሣጽ አትናቅ፤
በዘለፋውም አትመረር፤
12 አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣሁሉ፣
እግዚአብሔርምየሚወደውን ይገሥጻልና።
13 ጥበብን የሚያገኛት፣
ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው ቡሩክ ነው፤
14 እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣
ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና።
15 ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናት፤
አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም።
16 በቀኝ እጇ ረጅም ዕድሜ አለ፤
በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች።
17 መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤
ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው።
18 ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤
የሚይዟትም ይባረካሉ።
19 እግዚአብሔርበጥበብ ምድርን መሠረተ፤
በማስተዋል ሰማያትን በየስፍራቸው አጸና፤
20 በዕውቀቱ ቀላያት ተከፈሉ፤
ደመናትም ጠልን አንጠበጠቡ።
21 ልጄ ሆይ፤ ትክክለኛ ፍርድንና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤
እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፤
22 ለነፍስህ ሕይወት፣
ለዐንገትህም ጌጥ ይሆናሉ።
23 ከዚያም መንገድህን በሰላም ትሄዳለህ፤
እግርህም አይሰናከልም፤
24 ስትተኛ አትፈራም፤
ትተኛለህ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል።
25 ድንገተኛን መከራ፣
በክፉዎች ላይ የሚደርሰውንም ጥፋት አትፍራ፤
26 እግዚአብሔርመታመኛህ ይሆናልና፤
እግርህንም በወጥመድ ከመያዝ ይጠብቃል።
27 ማድረግ እየቻልህ
ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ።
28 አሁን በእጅህ እያለ፣
ጎረቤትህን፣ “ቈይተህ ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው።
29 አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በተቀመጠ፣
በጎረቤትህ ላይ ክፉ አትምከርበት።
30 ምንም ጒዳት ሳያደርስብህ፣
ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ።
31 በክፉ ሰው አትቅና፤
የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ፤
32 እግዚአብሔርጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤
ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል።
33 የእግዚአብሔርርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤
የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል።
34 እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤
ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።
35 ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤
ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል።