ሰባቱ መላእክትና ሰባቱ መቅሠፍቶች
1 ሌላም ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ የመጨረሻዎቹን ሰባት መቅሠፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት አየሁ፤ የመጨረሻ የተባሉትም የእግዚአብሔር ቊጣ የሚፈጸመው በእርሱ በመሆኑ ነው።
2 ከእሳት ጋር የተቀላቀለ የብርጭቆ ባሕር የሚመስል አየሁ፤ በባሕሩም አጠገብ አውሬውን፣ ምስሉንና የስሙን ቊጥር ድል የነሡትን ቆመው አየሁ፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን በገና ይዘው፣
3 የእግዚአብሔር ባሪያ የሆነውን የሙሴን መዝሙርና የበጉን መዝሙር እንዲህ እያሉ ይዘምሩ ነበር፤
“ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሆይ፤
ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው።
የዘመናትንጉሥ ሆይ፤
መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው።
4 ጌታ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ፣
ስምህን የማያከብርስ ማን ነው?
አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና።
የጽድቅ ሥራህ ስለ ተገለጠ፣
ሕዝቦች ሁሉ ይመጣሉ፤
በፊትህም ይሰግዳሉ።
5 ከዚህ በኋላም አየሁ፤ በሰማይ ያለው ቤተ መቅደስ፣ ይኸውም የምስክሩ ድንኳን ተከፍቶ ነበር፤
6 ሰባቱን መቅሠፍቶች የያዙት ሰባቱ መላእክት ከቤተ መቅደሱ ወጡ፤ እነርሱም ከተልባ እግር የተሠራ ንጹሕ የሚያበራ ልብስ ለብሰው፣ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጥቀው ነበር።
7 ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን አንዱ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚኖረው አምላክ ቊጣ የተሞሉትን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው።
8 ቤተ መቅደሱም ከእግዚአብሔር ክብር፣ ከኀይሉም በወጣው ጢስ ተሞላ፤ የሰባቱ መላእክት ሰባት መቅሠፍቶች እስኪፈጸሙ ድረስ ማንም ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት አልቻለም።