ሰቆቃወ 1

1 በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ፣

እንዴት የተተወች ሆና ቀረች!

በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው፣

እርሷ እንዴት እንደ መበለት ሆነች!

በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፣

አሁን ባሪያ ሆናለች።

2 በሌሊት አምርራ ታለቅሳለች፤

እንባዋ በጉንጮቿ ላይ ይወርዳል፤

ከወዳጆቿ ሁሉ መካከል፣

የሚያጽናናት ማንም የለም፤

ባልንጀሮቿ ሁሉ ከድተዋታል፤

ጠላቶቿም ሆነዋል።

3 በመከራና በመረገጥ ብዛት

ይሁዳ ተማርካ ሄደች፤

በሕዝቦችም መካከል ተቀመጠች፤

የምታርፍበትንም ስፍራ አጣች፤

በጭንቀቷ መካከል ሳለች፣

አሳዳጆቿ ሁሉ አገኟት።

4 የጽዮን መንገዶች ያለቅሳሉ፤

በዓላቷን ለማክበር የሚመጣ የለምና፤

በበሮቿ ሁሉ የሚገባና የሚወጣ የለም፤

ካህናቷ ይቃትታሉ፤

ደናግሏ ክፉኛ አዝነዋል፤

እርሷም በምሬት ትሠቃያለች።

5 ባላጋሮቿ ገዦቿ ሆኑ፤

ጠላቶቿ ተመችቶአቸዋል፤

ከኀጢአቷ ብዛት የተነሣ፣

እግዚአብሔርከባድ ሐዘን አምጥቶባታል።

ልጆቿ በጠላት ፊት ተማርከው፣

ወደ ግዞት ሄደዋል።

6 የጽዮን ሴት ልጅ፣

ግርማ ሞገሷ ሁሉ ተለይቶአታል፤

መሳፍንቶቿ፣

መሰማሪያ እንዳጣ ዋልያ ናቸው፤

በአሳዳጆቻቸው ፊት፣

በድካም ሸሹ።

7 በተጨነቀችባቸውና በተንከራ ተተችባቸው ቀናት፣

ኢየሩሳሌም በጥንት ዘመን የነበራትን፣

ሀብት ሁሉ ታስባለች፤

ሕዝቦቿ በጠላት እጅ በወደቁ ጊዜ፣

የረዳት ማንም አልነበረም፤

ጠላቶቿ ተመለከቷት፤

በመፈራረሷም ሣቁ።

8 ኢየሩሳሌም ከባድ ኀጢአት ሠርታለች፤

ስለዚህም የረከሰች ሆናለች፤

ያከበሯት ሁሉ ናቋት፤

ዕራቍቷን ሆና አይተዋታልና፤

እርሷ ራሷ ታጒረመርማለች፤

ወደ ኋላዋም ዘወር ብላለች።

9 ርኵሰቷ በቀሚሷ ላይ ታየ፤ ወደ ፊት የሚሆንባትን አላሰበችም፤

አወዳደቋ አስደንጋጭ ሆነ፤

የሚያጽናናትም አልነበረም፤

“እግዚአብሔርሆይ፤ መከራዬን

ተመልከት፤

ጠላት ድል አድርጎአልና!”

10 በሀብቷ ሁሉ ላይ፣

ጠላት እጁን ዘረጋ፤

ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ፣

የከለከልሀቸው፣

ጣዖት የሚያመልኩ አሕዛብ፣

ወደ መቅደሷ ሲገቡ አየች።

11 እንጀራ በመፈለግ፣

ሕዝቧ ሁሉ በሥቃይ ይጮኻል፤

በሕይወት ለመኖር፣

የከበረ ሀብታቸውን በምግብ ይለውጣሉ፤

“አቤቱእግዚአብሔርሆይ፤ አስበኝ፤ ተመልከተኝም፤

እኔ ተዋርጃለሁና።”

12 “እናንት መንገድ ዐላፊዎች ሁሉ፤ ይህ ለእናንተ ምንም አይደለምን?

ተመልከቱ፤ እዩም፤

በጽኑ ቍጣው ቀን፣

እግዚአብሔርያመጣብኝን፣

በእኔ ላይ የደረሰውን፣

የእኔን መከራ የመሰለ መከራ አለን?

13 “ከከፍታ ስፍራ እሳትን ላከ፤

ወደ ታች ወደ ዐጥንቶቼም ሰደደው፤

በእግሮቼ ላይ መረብ ዘረጋ፤

ወደ ኋላም ጣለኝ፤

ቀኑን ሙሉ በማድከም፣

ባዶ አድርጎ አስቀመጠኝ።

14 “ኀጢአቶቼ ቀንበር ሆኑ፤

በእጆቹ አንድ ላይ ተገመዱ፤

በዐንገቴም ላይ ተጭነዋል፤

ኀይሌንም አዳከመ፤

ልቋቋማቸው ለማልችላቸው፣

እርሱ አሳልፎ ሰጠኝ።

15 “በውስጤ ያሉትን ተዋጊዎች ሁሉ፣

እግዚአብሔር ተቃወመ፤

ጒልማሶቼን ለማድቀቅ፣

ሰራዊት በላዬ ላይ ጠራ፤

ድንግሊቱን የይሁዳ ሴት ልጅ፣

እግዚአብሔር በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረገጣት።

16 “የማለቅሰው ስለ እነዚህ ነገሮች ነው፤

ዐይኖቼ በእንባ ተሞልተዋል፣

ሊያጽናናኝ የቀረበ፣

መንፈሴንም ሊያረጋጋ የሞከረ ማንም የለም፤

ጠላት በርትቶአልና

ልጆቼ ተጨንቀዋል።”

17 ጽዮን እጆቿን ዘረጋች፤

የሚያጽናናትም የለም፤

ጎረቤቶቹ ጠላቶቹ እንዲሆኑ፣

እግዚአብሔርበያዕቆብ ላይ ትእዛዝ አውጥቶአል፤

ኢየሩሳሌምም በመካከላቸው፣

እንደ ርኵስ ነገር ተቈጠረች።

18 “እግዚአብሔርጻድቅ ነው፤

እኔ ግን በትእዛዙ ላይ ዐመፅ አድርጌ ነበር፤

እናንተ ሕዝቦች ሁሉ ስሙ፤

መከራዬንም ተመልከቱ፤

ወይዛዝርቶቼና ጐበዛዝቶቼ፣

ተማርከው ሄደዋል።

19 “ወዳጆቼን ጠራኋቸው፤

እነርሱ ግን ከዱኝ፤

ካህናቶቼና ሽማግሌዎቼ፣

ሕይወታቸውን ለማትረፍ፣

ምግብ ሲፈልጉ፣

በከተማዪቱ ውስጥ አለቁ።

20 “አቤቱእግዚአብሔርሆይ፤ እንዴት ተጨንቄአለሁ!

በውስጤ ተሠቃይቼአለሁ፤

በልቤ ታውኬአለሁ፤

እጅግ ዐመፀኛ ሆኛለሁና፤

በውጭ ሰይፍ ይፈጃል፤

በቤትም ውስጥ ሞት አለ።

21 “ሰዎች የሥቃይ ልቅሶዬን ሰሙ፤

የሚያጽናናኝ ግን ማንም የለም፤

ጠላቶቼ ሁሉ ጭንቀቴን ሰሙ፤

አንተ ባደረግኸውም ደስ አላቸው፤

አቤቱ የተናገርኻት ቀን ትምጣ፤

እነርሱም እንደ እኔ ይሁኑ።

22 “ክፋታቸው ሁሉ በፊትህ ይቅረብ፤

ከኀጢአቴ ሁሉ የተነሣ፣

በእኔ ላይ እንዳደረግኽብኝ፣

በእነርሱም ላይ አድርግባቸው፤

የሥቃይ ልቅሶዬ በዝቶአል፤

ልቤም ደክሞአል።”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *